አብርሆት ቤተ መጽሐፍት ለልጆች ምን ይዟል?

You are currently viewing አብርሆት ቤተ መጽሐፍት ለልጆች ምን ይዟል?

ልጆች እንዴት ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ሁሉም መልካም እንደነበር ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ልጆችዬ፤ ዛሬ አጭር ቆይታ የምናደርገው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስለሚገኘው የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት መረጃዎችን በመለዋወጥ ነው፡፡

አብርሆት ቤተ መጽሐፍት በተለምዶ አራት ኪሎ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ይገኛል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አስር ቤተ መፃህፍት አንዱ ነው፡፡ በአራት ወለሎች ተከፍሎ በውስጡ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን መጽሐፍት የሚይዝ መደርደርያ ተገጥሞለታል፡፡ ከ240 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወረቀት አልባ መጽሐፍትና 300 ሺህ ጥናታዊ ፅሑፎች በውስጡ ይዟል፡፡

የህፃናት ማንበብያ ስፍራን ጨምሮ የአይነ ስውራን ማንበቢያ ቦታና የብሬል መጽሐፍት ይገኙበታል፡፡ አምፊ ቴአትር እና መጫዎቻ ስፍራዎች እንዲሁም ከ120 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ መመገቢያ ካፌ፣ ስምንት የመጽሐፍትና ተጓዳኝ አገልግሎት መስጫ ሱቆች ይገኙበታል፡፡

ሰፊ እና ብዙ ክፍሎች ባለው መጽሐፍት ቤቱ ውስጥ ብዙ ሰዎች በየቀኑ እየመጡ መጽሐፍትን ያነብባሉ። መጽሐፍት ቤቱ ቅጥር ግቢው በአበቦች የተዋበ እና ንፅህናውም ቢሆን እናንተ ልጆች ጭምር ልትወዱት የምትችሉት አይነት ነው፡፡

ታዲያ ልጆች አጠቃላይ ሁኔታውም ሆነ ውጫዊ ገጽታው በዚህ ልክ ለመግለጽ የሞከርነው አብርሆት ቤተ መጽሐፍት ለእናንተ ለልጆች የሚሆን የንባብ ክፍልም አለውና እሱን እናስቃኛችኋለን። የምናስቃኛችሁ እድሜያችሁ ከ3 ዓመት እስከ 10 ዓመት የእድሜ ክልል ለምትገኙ ልጆች ነው፡፡

በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ወደ ልጆች ንባብ ክፍል ከማቅናታችን በፊት ዋናውን የቤተ መጽሐፍቱን በር አልፈን እንደገባን ከፊት ለፊታችን፣ በስተግራ በኩል የቤተ መጽሐፍቱን ሠራተኞች እናገኛለን። እነሱ ወዳሉበት ጠረጴዛ በመጠጋት መረጃዎችን እንጠይቃለን፡፡ እነሱም ስለ ቤተ መጽሐፍቱ እያንዳንዱን ነገር ስለሚያውቁ በትህትና የምንፈልገውን ይነግሩናል፡፡ በቤተ መጽሐፍቱ ብዙ የተለያዩ  መጽሐፍቶች አሉ፡፡ እነዚህን መጽሐፍት የት እንደሚገኙ ጭምር እነዚህ ሠራተኞች ያውቃሉ፡፡

ሠራተኞቹ ጥያቄያችሁን እንደተቀበሉ ይዘዋችሁ ወደ ልጆች ማንበቢያ ክፍል ይሄዳሉ፡፡ ወደ ክፍሉ እንደገባችሁ በተለያየ ቀለማት ያጌጡ ምቹ ወንበሮች እና የማንበቢያ ጠረጴዛዎች ይገኛሉ፡፡

በመጽሐፍት ቤቱ የተለያየ ይዘት ያላቸው መጽሐፍቶች አሉ፡፡ በተለይ ስለ ሀገራችን ታሪክ፣ ባህል፣ ሕዝቦች የተፃፉ በርካታ መጽሐፍቶች አሉ፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ ከእነዚህ  መካከል የተረት መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቋንቋ የተፃፉ ተረቶች እንዲሁም እውቀትን የሚያስገበዩ የመማሪያ መጽሐፍቶች ይገኛሉ፡፡ ስለ ህዋ ሳይንስ የተፃፉም በንባብ ክፍሉ ይገኛሉ፡፡

ልጆች፤ በማንበቢያ ክፍሉ ውስጥ የተለያዩ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው መጽሐፍትም  አሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ልጆች መጽሐፍቶቹን ስታነብቡ መንፈሳዊ እድገታችሁ ከፍ እንዲል ስለሚያግዟችሁ ነው፡፡ ልጆች፤ ፈጣሪያችሁን ፈርታችሁ፣ እናት አባታችሁን አክብራችሁ፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁን እና አስተማሪዎቻችሁን በፍቅር ወድዳችሁ ለመኖር መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውን መጽሐፍት ማንበብ ይጠቅማችኋል፡፡

ሌላው በቤተ መጽሐፍቱ ውስጥ ከገባችሁ በኋላ ወደ ቤታችሁ ቶሎ እንዳትሄዱ የሚያደርጓችሁ ነገሮች ሁሉ የተሟሉለት መሆኑ ነው፡፡ በንባብ ክፍል ውስጥ  ውሃ እንዳይጠማችሁ በማሰብ የተዘጋጀ ንፁህ ውሃ አለ፡፡ ለእናንተ ብቻ የተዘጋጀ የመፀዳጃ አገልግሎት የምታገኙበት ክፍሎችም አሉ፡፡

ልጆች ወደ ቤተ መጽሐፍት ቤቱ ከሰኞ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት መጥታችሁ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡ ቅዳሜ በተለየ ሁኔታ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት  እስከ 6፡00 ሰዓት ልዩ መርሀ ግብር አለ፡፡ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች መጥተው የስዕል ስራዎችን በፈለጋችሁት አግባብ መሳል ትችላላችሁ፣ ተረቶች ይነበባሉ፣ የቀለማቶች ቀን እና መሰል የተለያዩ ሁነቶች ይካሄዳሉ፡፡ በተጨማሪም በበዓላት ቀን የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት  አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review