አትሌት ጀማል ይመር እና ፍቅርተ ወረታ የባለፈው ዓመት የሴኡል ድላቸውን ለመድገም ከነገ በስቲያ ይሮጣሉ

You are currently viewing አትሌት ጀማል ይመር እና ፍቅርተ ወረታ የባለፈው ዓመት የሴኡል ድላቸውን ለመድገም ከነገ በስቲያ ይሮጣሉ

AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም

ከኮሪያ ብቸኛው የፕላቲኒዬም ደረጃ የተሰጠው የሴኡል ማራቶን ከነገ በስቲያ (እሁድ) ይደረጋል፡፡

የባለፈው ዓመት አሸናፊዎቹ ጀማል ይመር እና ፍቅርተ ወረታ ድላቸውን ለማስጠበቅ የማሸነፍ ግምት ያገኙ አትሌቶች ናቸው፡፡

የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድርን ሁለት ጊዜ በብር ሜዳሊያ ያጠናቀቀው ጀማል ይመር፣ ባለፈው ዓመት የሴኡል ማራቶንን ሲያሸንፍ የገባበት 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ የራሱ ምርጥ ሰዓት ነው፡፡

በቅርቡ የተካሄደውን የሂውስተን ግማሽ ማራቶንን አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀወ ጀማል እሁድ ሶስተኛ ማራቶኑን ለመሮጥ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የደቡብ ኮሪያ መገናኘ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ኬንያውያን አትሌቶች ቀላል ግምት አልተሰጣቸውም፡፡

በ2021ዱ የአምስተርዳርም ማራቶን ያስመዘገበው 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ09 የራሱ ፈጣን ሰዓት የሆነለት በርናርድ ኪፕሮፕ ኮች ቀዳሚው ነው፡፡

ሴኡል ላይ ከሚሮጡ አትሌቶች መካከል ፈጣን ሰዓት ያለው ኮች፣ ፊሊሞን ኪፕቹምባ፣ ሰለሞን ኪርዋ ዬጎ እንዲሁም የመጀመሪያ ማራቶኑን የሚሮጠው ኢቤንዮ የጀማል ይመር ዋነኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ተገምተዋል፡፡

ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ሃፍቱ ተክሉም የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡

ገብረጻዲቅ አብረሃ፣ አሸናፊ ሞገስ፣ አዳነ ከበደና ክብሮም ደስታ ከ2 ሰዓት ከ08 በታች ይዘው ሴኡል ላይ የሚሮጡ ሌሎች አትሌቶች ናቸው፡፡

የሴቶቹም ውድድር ከኢትዮጵያውያን እንደማይወጣ ተገምቷል፡፡

ፍቅርተ ወረታ ቀዳሚዋ ተገማች ናት፡፡

የባለፈው ዓመቱን የሴኡል ማራቶን ስታሸንፍ የወሰደባት 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ 32 ሰከንድ የራሷ ምርጥ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡

ከሁሉም ተወዳዳሪዎች ፈጣን ሰዓት ያላት መስታዋት ፍቅር ናት፡፡

መስከረም ወር ላይ የበርሊን ማራቶንን በሁለተኛት ስታጠናቅቅ 2 ሰዓት ከ18 ደቂ ከ48 ሰከንድ የወሰደባት መስታዋት፣ ቀዳሚዋ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት፡፡

የባለፈው ዓመቱን ፓሪስ ማራቶን ያሸነፈችው መስታዋት ፍቅር በቦስተን ግማሽ ማራቶንም ሁለተኛ ሆና ነበር የጨረሰችው፡፡

የበርሊን ማራቶንን በሶስተኛት ስታጠናቅቅ 2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ብቻ የወሰደባት ቦሰና ሙላቴ ከሴኡል ማራቶን ተሳታፊዎች ሁለተኛዋ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት፡፡

ቤተልሄም አፈንጉስ እና በቀለች ጉደታ ሌሎች ሴኡል ላይ የሚጠበቁ አትሌቶች መሆናቸውን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review