AMN – ጥር- 23/2017 ዓ.ም
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ከሩስያ ዩናይትድ ፓርቲ ሱፕሪም ካውንስል ቢሮ አባልና የሩስያ ፌዴሬሽን ሴናተር አንድሬ ክሊሞቭ ጋር ተወያዩ
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በተለይም በአረንጓዴ ልማት፣ በግብርና፣ ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች የተሳካ ልማት እያከናወነችና ፈጣን ዕድገትም እያስመዘገበች መሆኑን አቶ አደም ገልጸዋል።
ለዚህ የልማት ስኬትም የህዝብ ጠንካራ ተሳትፎና ትብብር የታከለበት መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን በማጠናከር ሚናዋን የበለጠ እንድትወጣ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ነው ያነሱት።
የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር እና የሴኔቱ ውጭ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ አንድሬይ ክሊሞቭ፤ ሁለቱ አገራት ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸ አንስተው፥ በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ በመጋበዛችን የላቀ አክብሮትና ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።
ኢትዮጵያና ሩሲያ በተለይም በአቅም ግንባታ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን በግብርና፣ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች የትብብር ግንኙነታቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።