
AMN ኅዳር – 29/2017 ዓ.ም
አንድ ሰው ኢትዮጵያን ለማወቅ ብዙ ብሔሮችን በጥልቀት ማስተዋል እና መማር ይጠበቅበታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባምንጭ ከተማ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ ቤተ መጽሐፍት ናት ሲሉ ገልጸዋታል።
ቤተመጽሐፍትን በምሳሌነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቤተመጽሐፍት በውስጡ በርካታ መጽሐፍትን በመያዙ ከአንድ መጽሐፍ እንደሚበልጥ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም አንድ መጽሐፍ ከማንበብ በአንድ ቤተመጽሐፍት መገልግል የበለጠ የእውቀት ባለቤት ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም እንደ ትልቅ ቤተመጽሐፍት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በውስጧም ልዩ ልዩ ታሪኮች፡ ቋንቋዎች፡ እውቀቶች እና ጥበቦች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እነዚህን እውቀቶች እና ጥበቦች በተናጠል ከመገልግል በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ በሙሉነት ማየት ይበልጥ የሚያጠናክር እና የሚያሻግር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማየት ከአንድ መጽሐፍ በላይ በቤተመጽሐፍት መገልገል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አንድ መጽሐፍ ብቻውን ሙሉ አይደልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱ መጽሐፍ ከብዙ መጽፍቶች የተቀዳ መሆኑን አንስተዋል።
እያንዳንዱ ብሄር ብቻውን ሙሉ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከእያንዳንዱ ብሄር ወግ፡ ማዕረግ፡ ቋንቋ እና ባህል ይሰንቃል ይማራል ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ሰው መጽሐፍ ሲጽፍ በርካታ መጽሐፍትን ማገላበጥ እንዳለበት ሁሉ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ለመሰኘት እና ኢትዮጵያን ለማወቅ ብዙ ብሔሮችን በጥልቀት ማስተዋልና መማር እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል።
መላው ኢትዮጵያዊያን ልባቸውን ወደ ሰላምና ፍቅር በመመለስ ኢትዮጵያን ለማወቅና ለማበልጸግ በጋራ እንዲሰሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰፊና ሁሴን