አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የከተማዋን የብዝሃነት ባህሪ ያገናዘበ አቀራረብ ይዞ መምጣቱ ተገለፀ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የከተማዋን የብዝሃነት ባህሪ ያገናዘበ አቀራረብ ይዞ መምጣቱ ተገለፀ

• ሚዲያው ኤኤምኤን ፕላስ በተሰኘው ሁለተኛው የቴሌቪዥን ቻናሉ በተለያዩ ቋንቋዎች ከዛሬ ታህሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የመደበኛ ስርጭቱን ይጀምራል

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የአዲስ አበባ ከተማን የብዝሃነት ባህሪ ያገናዘበ አቀራረብ ይዞ መምጣቱ ተገለፀ

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፤ ኤኤምኤን ፕላስ የተሰኘው ተጨማሪ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭት የሚጀምር መሆኑን አስመልክቶ እንደተናገሩት፣ ከተማዋ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሚኖሩባት እንደመሆኗ ይህን ባህሪ ያገናዘበ አቀራረብ ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከተማዋ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መናገሻ እንደሆነች ያወሱት አቶ ካሳሁን፣ በመሆኑም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በይዘት፣ በአደረጃጀትና መሰል ስራዎች ይህን ብዝሃነት ያገናዘበ ተግባር በመከወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ

የብዝሀነት ሚናችንን መወጣት ይኖርብናል ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ስለሆነም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በ5 የአገር ውስጥ እና በሁለት የዓለም አቀፍ ቋንቋዎች እየሰራ እንደሚገኝና ይህም በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎችም የስርጭት አድማሱን እያሰፋ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

አቶ ካሳሁን በገለፃቸው፣ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ደንበኞች ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ በፍላጎቱ ልክ የአየር ሰዓት ለማስፋት እየተሰራ ነው፡፡ በመሆኑም ከመደበኛው ቻናል በተጨማሪ ኤኤምኤን ፕላስ የተሰኘው ቻናል ዛሬ ታህሳስ  21 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ስርጭ ይገባል ብለዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን በ2023 ሜትሮ ፖሊታን ሚዲያ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም የአምስትና የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ዋነኛው የሚዲያው ትኩረት ትውልድ ላይ መስራት ነው ብለው፣ በመሆኑም አገሩን የሚወድድና ለአገሩ የሚሰራ ትውልድ ማፍራት ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አቀራረቦችና ይዘቶችም ከዚህ አንጻር የተቃኙ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡

ለቋንቋዎች ተጨማሪ የአየር ሰዓት በመፍጠር ቴክኖሎጂና ፈጠራ ታክሎበት እውነተኛ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭ ሚዲያ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ 

ሚዲያው በለውጥ ሂደት ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ የሁለተኛው የቴሌቪዥን ቻናል ኤኤምኤን ፕላስ መጀመር ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩን ሲያብራሩም፣ በክልሎችና በህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ድርሻው ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

የኤኤምኤን ፕላስ ወደ ስርጭት መግባት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በዲጂታልና ህትመት ተወዳዳሪ፣ ተመራጭና ተደራሽ ለመሆን የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ባህሪ አንጻር ሚዲያው መምሰል ያለበት ይህንኑ በመሆኑ ሁለተኛውን የቋንቋዎች ቻናል መክፈት ማስፈለጉን አብራርተዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ መቀመጫ እንደመሆኗ ይህንን ያገናዘበ መልክና ቁመና እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፈጠራ ያለው፣ ተወዳዳሪና ገቢውን የሚያሳድግ ጭምር ስለመሆኑ አንስተው የቻናሉ መከፈት ብዙ ጥያቄዎችን ይመልሳል፡፡ ለሁሉም ዕድል መስጠት ከማስቻሉም በላይ አዲስ አበባ ላይ የሚከሰቱ ጉዳዮች ኢትዮጵያን የሚገልጹ በመሆናቸው አስተዋጽኦው ትልቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ቻናሉ ልክ አንደመደበኛው ቻናል ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተናግድ በመሆኑ ለብዙዎች መድረስ ያስችላል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚያዩትና የሚያዳምጡት ብቻ ሳይሆን የሚሳተፉበትና ሀሳባቸውን የሚገልጹበት ነውና የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና የስራ ኃላፊዎች ተሳትፏቸውን ከዚህም በላይ እንዲያጠናክሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተለይም የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በሚዲያዎቹ እንዲያስተዋውቁ ጥሪያቸውን አቅርበው፣ ሚዲያው በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ ለማመላከት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በይዘት፣ በአቀራረብና በቴክኖሎጂ ተደራሽነት ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የሪፎርም ስራዎቹ ከከተማ ሚዲያ ባህሪ አንጻር ሲመዘኑም የተለያዩ ቋንቋዎችን ለማስተናገድም እየተደረገ ያለው ጥረት ከዚህም በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review