አዲስ አበባ ለፈጠራ ስራ ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በሶስተኛው ዙር ብሩህ አዲስ የንግድ ሀሳብ ፈጠራ የፍፃሜ ውድድር ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።
ሶስተኛው ዙር ብሩህ አዲስ የንግድ ሀሳብ ፈጠራ የፍፃሜ ውድድር “የሀሳብ ፈጠራ ለብሩህ ነገ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በውድድሩ የቀረቡ ሁሉንም የፈጠራ ሀሳቦች ከተማ አስተዳደሩ በየዘርፉ እንደሚጠቀምባቸው የገለፁት አቶ ጃንጥራር፣ ይህም በቀጣይ የሚተገበር ይሆናል ብለዋል።
አዲስ አበባ ተወዳዳሪ ብሎም ተመራጭ ለመሆን እየሰራች ካለችው ሰፊ የልማት ስራ በተጨማሪ፣ የሀሳብ ፈጠራዎችንና ፈጣሪዎችን በማወያየት፣ በማሰልጠን፣ በማወዳደርና በመሸለም ሀሳባቸውን ወደ ተግባር እየቀየርን እንገኛለን በማለትም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሌም ቢሆን ለስራ ፈጠራ የቅድሚያ ቅድሚያ እንደሚሰጥና ሁሌም ከስራ ፈጣሪዎች ጎን እንደሚሆን አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል።
በንጉሱ በቃሉ