አዲስ አበባ ለፈጠራ ስራ ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በሶስተኛው ዙር ብሩህ አዲስ የንግድ ሀሳብ ፈጠራ የፍፃሜ ውድድር ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።
ሶስተኛው ዙር ብሩህ አዲስ የንግድ ሀሳብ ፈጠራ የፍፃሜ ውድድር “የሀሳብ ፈጠራ ለብሩህ ነገ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በውድድሩ የቀረቡ ሁሉንም የፈጠራ ሀሳቦች ከተማ አስተዳደሩ በየዘርፉ እንደሚጠቀምባቸው የገለፁት አቶ ጃንጥራር፣ ይህም በቀጣይ የሚተገበር ይሆናል ብለዋል።
አዲስ አበባ ተወዳዳሪ ብሎም ተመራጭ ለመሆን እየሰራች ካለችው ሰፊ የልማት ስራ በተጨማሪ፣ የሀሳብ ፈጠራዎችንና ፈጣሪዎችን በማወያየት፣ በማሰልጠን፣ በማወዳደርና በመሸለም ሀሳባቸውን ወደ ተግባር እየቀየርን እንገኛለን በማለትም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሌም ቢሆን ለስራ ፈጠራ የቅድሚያ ቅድሚያ እንደሚሰጥና ሁሌም ከስራ ፈጣሪዎች ጎን እንደሚሆን አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ፣ ቢሮው የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣት ወጣቶች አዳዲስ የስራ ሀሳቦችን እንዲፈጥሩ በማድረግ ከራሱ አልፎ ለሀገር እንዲጠቅም ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት 11 ወራት ብቻ እንደ ከተማ ለ341 ሺህ ስራ ፈላጊዎች የመስሪያ ቦታ በመስጠትና ብድር እንዲያገኙ ከባንኮች ጋር በማስተሳሰር ወደ ስራ መግባት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።
የሀገር በቀል ፈጠራዎችንና የሀሳብ ባለቤቶችን በማበረታታት ችግር ፈች እንዲሁም ተመራጭ የሆኑ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ ሀሳቦችን ወደተግባር ማስገባት የውድድሩ ዓላማ መሆኑ ገልፀዋል።
እንደ ከተማ 145 ተወዳዳሪዎች የተለያዮ የስራ ሀሳቦችን ይዘው የተወዳዳሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ከ1 እስከ 15 የወጡ ተወዳዳሪዎች በፌደራል ደረጃ ለሚደረገው ውድድር ማለፋቸውን ተነግሯል።
በዛሬው ዕለት ከ15ቱ በተለያዮ ዙሮች ተመዝነው ለፍፃሜ የደረሱ 5 ተወዳዳሪዎች እየተወዳደሩ ይገኛሉ።
በፍፃሜው የውድድር መድረክ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
በንጉሱ በቃሉ