
AMN- ግንቦት 10/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖን(ETEX 2025) በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ተገኝተው መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ኤክስፖው ሀገራችን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በፊን-ቴክ እንዲሁም በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን እምቅ አቅም የሚያሳይ እና ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት እንዲሁም የተገኙ ስኬቶችን ለዓለም በማሳየት ብቁ ተተኪዎች ያሏት መሆኑን በግልፅ የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ አለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፍራንሶችን የማዘጋጀት ብቃቷ እየጨመረ የመጣ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ባለፉት አስር ቀናት ብቻ የአፍሪካ የፖሊስ ኮንፍራንስ፣ የሳይበር ሴክዩሪቲ ኮንፍራንስ፣ የአፍሪካ ደህንነት ኮንፍራንስ፣ የፋይናንሻል ኮንፍራንስ፣ የ AI ኮንፍራንስ ማካሄድ መቻሉን አውስተዋል፡፡

በነገው እለት ደግሞ የአይዲ ፎር አፍሪካ እና የILO ኮንፍራንስ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
ይህም የከተማዋን ገቢ ከመጨመር በተጨማሪ የኮንፍራንስ እና የቱሪዝም መዳረሻነቷን ከፍ በማድረግ እንዲሁም በተለያየ መንገድ ለነዋሪዎች የስራ እድል የከፈተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ እና ስማርት አዲስ አበባን እውን ለማድረግ የተፈጠረዉ አቅም የታየበት በመሆኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል::
