AMN – መጋቢት 10/2017
አዲስ አበባን ስማርት ሲቲ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴከኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ቱሉ ጥላሁን ተናገሩ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ቱሉ ጥላሁን ከኤኤምኤን ‘የሃሳብ ሚዛን’ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባን ስማርት ሲቲ እና ዘመናዊ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የምትችል ከተማ የማድረግ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት አገልግሎቶች የዘመኑ እና የቴክኖሎጂ አሰራርን ማዕከል ያደረጉ እንደሆነም አብራርተዋል።
ለአብነትም በገቢዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት፣ የመሬት አስተዳደር ፣ በፍትህ ተቋማት እንዲሁም በሌሎች ለማህበረሰቡ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ ቢሮው የዘመኑ አሰራሮችን እየዘረጋ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን በተሰሩት የኮሪደር ልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማእከል ያደረጉ ሰው ተኮር ስራዎች በስፋት መሰራታቸውን አውስተዋል፡፡
በሁሉም ተቋማት የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የቴክኖሎጂ አገልግሎትን ማእከል ያደረጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ቱሉ በተለይም የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት ለዚህ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና ወጣቱ ከቴክኖሎጂ ጋር ትውውቅ እና ቁርኝት እንዲኖረው እንዳስቻለ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ አበባ በአለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ እና የስማርት ሲቲ ከተማን ባህሪ የተላበሰች እንድትሆን ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋልም ብለዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ