‹‹አዴሞላ ሉክማን ከዓለማችን ደካማ ፍጹም ቅጣት ምት መቺዎች አንዱ ነው››

You are currently viewing ‹‹አዴሞላ ሉክማን ከዓለማችን ደካማ ፍጹም ቅጣት ምት መቺዎች አንዱ ነው››

ጂያንፔሮ ጋስፔሪኒ

AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ዘንድሮ ገቢራዊ ባደረገው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ቅርጽ እስከ ስምንተኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ያልጨረሰው አታላንታ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ትናንት ከመድረኩ ተሰናብቷል፡፡

የጣሊያኑ ክለብ ከቤልጄየሙ ክለብ ብሩዥ ጋር ያደረገውን የደርሶ መልስ የቅድመ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ 5ለ2 ተሸንፎ ነው ከውድድሩ የተባረረው፡፡ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታውን ቤልጂየም ላይ አድርጉ 2ለ1 ተሸንፎ የተመለሰው አታላንታ ትናንት ምሽት የመልስ ጨዋታውን በሜዳው አድርጎ 3ለ1 ተረቷል፡፡ በጨዋታው መሀል ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አዴሞላ ሉክማን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ከጨዋታው በኋላ ስለ ክስተቱ የተጠየቁት አንጋፋው አሰልጣኝ ጂያንፔሮ ጋስፔሪኒ ‹‹አዴሞላ ሉክማን ከዓለማችን ደካማ ፍጹም ቅጣት ምት መቺዎች መካከል አንዱ ነው›› ብለዋል፡፡ የመጀመሪያዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ፍጹም ቅጣት ምት ስናገኝ ኳሷን ቀድሞ ያዘ፣ መታና ሳተ ለምን ይህንን እንዳደረገ አላውቅም ብለዋል ጋስፔሪኒ ስለ ናይጄሪያዊ አጥቂ ሲጠየቁ፡፡

ሌላው የጣሊያን ክለብ ኤሲ ሚላንም ከመድረኩ ተሰናብቷል፡፡ ከኔዘርላንድሱ ፌይኖርድ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ያደረገው ኤሲ ሚላን 2ለ1 ተሸንፎ ከውድድሩ ተሸኝቷል፡፡ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታውን 1ለ0 የተሸነፈው ሚላን ትናንት ምሽት በሜዳው የመልሱን ጨዋታ አድርጎ 1ለ1 ተለያይቶ ነው ለስንብት የተዳረገው፡፡

ሚላን ጨዋታው እንደተጀመረ መሪ ያደረገችውን ግብ በሳንቲያጎ ዢሚኔዝ ቢያስቆጥርም ያልተገባ አጨዋወት (ፋወል) ሳይሰራበት ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ወድቆ ያጭበረበረው ቲኦ ኸርናንዴዝ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በመውጣቱ ብልጫ ተወስዶበት አቻ ተለያይቶ በድምር ውጤት ከመድረኩ ተሰናብቷል፡፡

ቤኔፊካና ሞናኮ የትናንት ጨዋታቸውን ሶስት አቻ ቢያጠናቅቁም በደርሶ መልስ ቤኔፊካ 4ለ3 አሸንፎ ሌላው ለጥሎ ማለፍ የበቃ ክለብ ሆኗል፡፡ ባየርን ሙኒክ በበኩሉ በ94ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ሴልቲክን በደርሶ መልስ 3ለ2 አሸንፎ የጥሎ ማለፍ ትኬቱን የቆረጠ ሌላኛው ክለብ ሆኗል፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review