አገልጋይነት፡- ሌላኛው አርበኝነት

You are currently viewing አገልጋይነት፡- ሌላኛው አርበኝነት

 “ወደኋላ መለስ አድርገን የተመለከትን እንደሆነ እኛ ኢትዮጵያውያን የበርካታ ድሎች ታሪክ ባለቤት ነን” የሚሉን በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ጽህፈት ቤት የነዋሪዎች ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግስት ተካልኝ ናቸው። ታሪክ ሰሪዎቹ አርበኞች ሀገር ሳትደፈር ከነ ሙሉ ክብሯ እንዳስረከቡን ሁሉ እኛ ደግሞ ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት የመፈፀም ግዴታ አለብን ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት በማብራሪያቸው፤ “በየፈርጁ ሊገለፅ የሚችለው የአርበኛነት ተጋድሎ የግድ የጦር መሳሪያ በመያዝ በሚደረግ ተጋድሎ ብቻ የሚገለጥ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተሰማራንበት የስራ መስክ ያለንን እውቀት አልያም የስራ ክህሎት በመጠቀም ተገልጋዩን ማህበረሰብ እንዳይማረር በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ እኔ በምሠራበት ተቋም አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮችን መተግበር ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለይም አንድ ተገልጋይ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የልደት የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት)፣ የጋብቻ ምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) እንዲሁም መሰል ጉዳዮችን ለማስፈፀም ባለጉዳዮች ወደ ጽህፈት ቤታችን ሲመጡ ምን ምን መስፈርቶች መሟላት እንዳለባቸው መረጃ የሚሰጥ በግልፅ ቦታ ላይ አስቀምጠናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“አርበኝነት ባለንበት የስራ መስክ ተገልጋይን በማርካት ይገለፃል” የሚሉት ወይዘሮ ትዕግስት፤ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተከወኑ በርካታ ተግባራቶች አሉ፡፡ ለማሳያነት ያክል ከዚህ ቀደም ወረፋ ለመያዝ ሌሊት በመምጣት ባለጉዳይ በብርድ ይንገላታ የነበረው አሁን የወረፋ መጠበቂያ ትኬት በመቁረጥ ብቻ በተራ ቁጥሩ መሰረት ይስተናገዳል። በመስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ አቅራቢያ “ምን ፈልገው መጡ? ጉዳይዎት በቀላሉ ይሰራሎታል፡፡” በሚል ገንዘብ የሚቀበሉ አካላት ነበሩ፡፡ ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ የተወሰደው ባለጉዳዮች በቀላሉ ከደላሎች እጅ እንዳይወድቁ ዩኒፎርም በለበሱ ባለሙያዎች ብቻ እንዲስተናገዱ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

 “እንደ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በተሰማራሁበት የስራ መስክ ለአገልግሎት አሰጣጡ መሳለጥ የሚጠበቅብኝን ሁሉ ማበርከት አለብኝ” የሚለን ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ጽ/ቤት የነዋሪዎች ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ባለሙያ ወጣት ዳንኤል ዘየደ ነው፡፡ የስራ ላይ አርበኝነት ስንል ተገልጋዩን ማህበረሰብ እንዴት መቀበል እንዳለብን የሚያሳይ ነው፡፡ “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንደሚባለው ባለጉዳዩ ያልተሟላ መረጃዎችን ይዞ ቢመጣ ምን ምን አሟልቶ መምጣት አለበት የሚለውን በትህትና የማስረዳት ኃላፊነት አለብኝ ብሏል፡፡

እንደ ወጣት ዳንኤል ገለፃ፤ አርበኝነት በተሰማራሁበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆንን ያጠቃልላል፡፡ አገልጋይነት የውስጥ ተነሳሽነትን ይጠይቃል፡፡ ዜጋን ማስደሰትና ማርካት የሚቻለው በሚሰጠው አገልግሎት ላይ እሴት መጨመር ሲቻል ነው፡፡ አለቃ አለ የለም የሚል አይነት ድብብቆሽ ውስጥ መግባት አይገባም፡፡ በዚህም ከሴክተሩ የስራ ባህሪ አንፃር የተከማቸ ስራ ስለነበር ለተገልጋዩ ፈጣን ምላሽ በመስጠት እርካታ ለማምጣት ሰዓት ከማክበር በዘለለ አዳር ሁሉ የሠራበት ጊዜ እንዳለ ያስታውሳል። ቅዳሜንና እሁድን ጭምሮ በመስራት የህብረተሰቡን እርካታ ከፍ ለማድረግ የተቻለውን ለማድረግ እየጣረ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ካሳ በማብራሪያቸው፣ “ጽህፈት ቤቱ በርካታ ባለጉዳይ የሚስተናገድበት ሲሆን በዋናነት የሚሰጠው አገልግሎት መሬት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ማገልገል ማለት በተሰጠኝ የስራ መስክ በቀናነት ብሎም በኃላፊነት ምላሽ በመስጠት ህብረተሰቡ ጋር የሚፈጠረውን ምልልስ መቀነስ መቻል ነው፡፡ ለሚሰራው ስራ የሚከፈለው ደሞዝ ከተገልጋዮች የሚገኝ ነው፡፡ ያንን በመረዳት የሚፈልጉትን አገልግሎት በተረጋጋ ሁኔታ መስጠት ከአገልጋይ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ጊዜውን የዋጀ አርበኛነት ማለት በመንግስት በተቀመጠው የስራ ሰዓት መስራት ነው። ከ2፡3ዐ ቀድመው ስራ ይጀምራሉ። ማታም ተገልጋይ እያለ ሰዓት ደረሰ ብለው አይወጡም፡፡ እሳቸውም ሆኑ ቤተሰባቸው አገልግሎት ፈልገው ሲሄዱ መጥፎ ነገር እንዲያጋጥማቸው እንደማይፈልጉት ሁሉ ተገልጋዮችን ፈገግ ብለው ይቀበላሉ፡፡ ቀናነት የተላበሰውን አገልግሎት “እንዴት አደራችሁ?” ብሎ ሰላምታ ከመስጠት ይጀምራሉ፡፡ ፈጣሪን ፈርተውና ስራቸውን አክብረው ይሰራሉ።

ደስ ብሎት የሚሄድ ባለጉዳይ እንዳለ ሁሉ ማሟላት ያለበትን ነገር ተነግሮት በድጋሜ እንዲመጣ የሚደረግ ባለጉዳይ ስለመኖሩ የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ሁሉንም ባለጉዳይ ከመመሪያው አንጻር እንደሚያስተናግዱ ተናግረዋል፡፡ “ትዕግስት በተሞላበት አግባብ ከመመሪያ አንፃር ለባለጉዳዩ የማስረዳት ኃላፊነት የአመራሩ ብሎም የባለሙያው ኃላፊነት ነው፡፡ በመመሪያው ላይ ‘የዜጎች ስምምነት ሰነድ ምን ይላል’ የሚለውን እስከማስገንዘብ የሚኬድበት ርቀት አለ። ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት መሬት ነክ የሆኑ ጉዳዮች በባህሪያቸው በደንብ ንግግርን የሚሹ በመሆናቸው ነው። ለዚህም ህግና ደንቡ ያስቀመጠውን መመሪያ በማሳየት በአገልግሎት አሰጣጡ ረክተው እንዲሄዱ ለማድረግ እሞክራለሁ” ብለዋል፡፡

ጽህፈት ቤታቸው የሚሰጠውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ምን ተሰራ ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ የአገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ተገልጋዮችን ማህደር በማደራጀት ወደ ሲስተም ማስገባት ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “እያንዳንዱ አገልግሎት ምን ያክል ግዜ ይፈጃል?” የሚለው በግልፅ በር ላይ ተለጥፏል፡፡ አገልግሎት ፈልጎ የሚመጣን አካል ለማስተናገድ የሚመጥን ምቹ ስፍራን የማስተካከል ስራም እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዜጎችን በቅንነት ማገልገል እንደ ተቋም የሚሰጠውን ጠቀሜታ አቶ ተስፋዬ ሲገልጹ፤ የተቋምን ርዕይና ተልእኮ ለማሳካት ያግዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ደንበኛን በዘላቂነት ለመያዝና የወጡ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች በአግባቡ ለመተግበርም እገዛው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

“ያለፉት አባቶቻችን ሀገርን ከውጭ ጠላት ለመከላከል ሲሉ በባዶ እግራቸው ተጉዘው፣ ደማቸውን ገብረው ሀገርን አፅንተዋል፡፡ እኛም ሀገርን ለመገንባት የምናበረክታቸው ጡቦች በእጃችን ላይ አሉን” የሚሉን ደግሞ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት አቶ ጅራ አመንቴ ናቸው፡፡ “የዓድዋን ድል ስናስብ የጀግንነትና የአርበኝነት ስሜቱን ይቀሰቅስልናል፡፡ ለዚህም ደግሞ የተማረው ማህበረሰብ ለሀገሩ እውቀቱን በተግባር በመከወን ቴክኖሎጂን መሰረት ባደረገ መልኩ መስራት አለበት። ዓለም የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ለመድረስ ዜጋው በተሰማራበት የሙያ መስክ ውጤታማ ተግባራትን መከወን ይጠበቅበታል፡፡ አክብሮትን፣ ትህትናን ብሎም ታዛዥነትን በማከል አገልጋይ መሆን አለበት” ብለዋል፡፡

እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አሁን ላይ 7/24 (ሰባቱንም ቀን ሀያ አራት ሰዓት) የስራ ባህልን በማዳበር ስራዎችን እየሠሩ ያሉ ተቋማት ስለመኖራቸው የሚናገሩት አቶ ጅራ፣ “የአርበኝነት አንዱ መገለጫ የስራ ሰዓትን ሳይሸራርፉ መስራት ነው። ያደጉ ሀገራት ዛሬ የደረሱበት ላይ መድረስ የቻሉት ካለምንም መዘናጋት ስራዎችን መከወን በመቻላቸው ነው፡፡ አንድ አገልግሎት ሰጪ ግለሰብ ስራውን የሚሰራው ለሰው ሳይሆን ለራሱ ሲል ነው፡፡ አርበኝነት በእድሜ፣ በፆታ፣ በሃብት እንዲሁም በእውቀት ደረጃ ልዩነት ሳይበጅለት ትህትናን በተላበሰ አግባብ ማስተናገድን ይጠይቃልም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አርበኝነት ዘርፈ ብዙ መገለጫ አለው። አንድ የመንግስት ሰራተኛ በተሰማራበት የሙያ መስክ በቅንነት ማገልገሉ ለሀገርና ተቋም ከሚሰጠው ጠቀሜታም ባለፈ ለራስ እና አገልግሎት ለሚሰጠው ግለሰብ የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያውና ዋናው የአእምሮ እርካታን ይሰጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ  ክብር ያስገኛል፣ ጓደኝነትን ወይንም ወዳጅነትን ይጨምራል፣  በቀጣይ አገልግሎት ተቀባይነትን ምቹ ያደርጋል፣ ጥሩ ስም እንደሚያስገኝም ተናግረዋል፡፡

አሁን ሀገራችንን በሙሉ አቅም የምናገለግልበት ወሳኝ ግዜ ላይ እንገኛለን የሚሉን የታሪክ ምሁሩ አቶ ጅራ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ሀገርን የመታደግ ኃላፊነት የነበረባቸው ሰዎች ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡ የዛሬ ትውልድ በተሰማራበት የሙያ መስክ ማህበረሰቡን ማገልገል ነው፡፡

መንግስት በቁርጠኝነት ስራዎችን ማከናወን የሚችለው ስራዎቻቸውን በአግባቡ ጠንቅቀው በሚሰሩ ቁርጠኛ የሀገር አርበኞች አማካኝነት ነው። ስራዎችን በባለቤትነት መንፈስ የሚከውኑ አካላትን ማበረታታት ቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ አቅም ለመፍጠር ያስችላል። ማህበረሰቡም ቢሆን የትኛውንም አገልግሎት ለማግኘት የመንግስትን በር ሲያንኳኳ መብቴ የትኛው ነው? ግዴታዬስ የትኛው ነው? በማለት ራሱን ማንቃት ይገባዋል፡፡ በዚህ ልክ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ከቻለ ሀገራችን ዓለም የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ለመድረስ ምንም የሚያግዳት ነገር አይኖርም የሚል እምነት አለኝ ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review