አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን እንዲኖራት ግልፅ አቋም ይዛለች – ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ

You are currently viewing አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን እንዲኖራት ግልፅ አቋም ይዛለች – ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ

AMN – የካቲት 8/2017 ዓ.ም

አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን እንዲኖራት ግልፅ አቋም መያዟን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ በበኩላቸው አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት በአግባቡ ውክልና እንዲኖራት እየሠራን ነው ብለዋል።

ይህ የተባለው ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።

ፕሬዚዳንት ታየ በሰጡት ማብራሪያ ትላንትና ዛሬ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ትላንት ከተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር የኢትዮጵያንና የመንግሥታቱ ድርጅትን የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ሀገራዊ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንና መግባባት ላይ መድረሳቸውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ ዛሬ ከመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ ጋር የጠቅላላ ጉባኤው ስልጣን እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ በነበረው የተመድ ሪፎርም ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በተለይም የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካን ያገለለ በመሆኑ ተገቢውን ውክልና በምታገኝበት ጉዳይ ላይ ጠቃሚ ሀሳቦች መለዋወጣቸውን ገልጸዋል።

ይህም እውን እንደሚሆን በውይይቱ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ መቀመጫ ማለትም ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን እና የአምስት ተለዋጭ አባልነት ስፍራ እንዲኖራት ግልፅ አቋም መያዟንም ጠቅሰዋል።

የቀድሞ የካሜሮን ጠቅላይ ሚኒስትርና የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ በበኩላቸው፥ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በነበራቸው ውይይት የተባበሩት መንግሥታትን እና አፍሪካን በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁልፍ የሆነች ሀገር ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ በተመድ ቻርተር በጽኑ የምታምን ወሳኝ አባል ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አክለውም አፍሪካ የማካካሻ ፍትሕ እንድታገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በተለይም በጸጥታው ምክር ቤት በአግባቡ ውክልና እንዲኖራት ለማድረግ አሁን መልካም አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰው፥ ተመድ የአፍሪካውያን ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ከመቀበል ባለፈ እየሰራበት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ዓም አቀፉ ማህበረሰብም በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም እንደሚኖረው አምናለሁ ሲሉ ነው የገለጹት።

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በይፋ በተጀመረበት ወቅት አፍሪካ የማካካሻ ፍትሕ እንድታገኝ እና በጸጥታው ምክር ቤት ተገቢው ውክልና እንዲኖራት ተጠይቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review