AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
አፍሪካዊያን እያጋጠሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን ለመቋቋም አንድነታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ አስገነዘቡ ፡፡
46ተኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ተጀምሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በአሁኑ ወቅት የባለብዙወገን የግንኙነት መስክ ከባድ ፈተና እያጋጠመው መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ለአፍሪካ የባለብዙ ወገን ግንኙነት መስክ ተመራጭ እና አስፈላጊ መሆኑን በንግግራቸው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ይኽ የግንኙነት ዘርፍ ምርጫችን የሚሆነው በትብብር፣በጋራ መግባባት እና አጋርነት ስለምናምን ነው ብለዋል።
አሁን ላይ እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ በመሆናቸው መፍትሔዎቻቸውም ዓለም አቀፍ እና የባለብዙወገን ግንኙነት ማዕቀፍን የሚሹ ናቸው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአካባቢ ብክለት፣የበርሃማነት መስፋፋት፣ወረረሽኝእና መሰል ዓለም አቀፍ የጤና ጉዳዮች በባለብዙወገን የትብብር ማዕቀፍ የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን እነዚህን መሰል ችግሮች ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣የአፍሪካ ሕብረት እና መሰል የባለብዙወገን መድረኮችን እና ተቋማትን ለማጠናከር የምናደርገውን ጥረት በዕጥፍ መጨመረ ይገባል ነው ያሉት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም እና በጸጥታ ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን፣የቴክኖሎጂ ለውጦች እና የጂኦ ፖለቲካዊ ፉክክሮች እያየሉ ምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን አፍሪካዊ አንድነት፣ ትብብር እና አጋርነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያሻ ነው ብለዋል።እንደ አሕጉር ዓለም አቀፍ ተቋማት፤ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክርቤትን ጨምሮ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ለአሕጉሪቷ ብልጽግና ትልቅ ተስፋ ሰጭ መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።ኢትዮጵያ ለአሕጉሩ ኢኮኖሚ ተስፋ ሰጭ በሆነው አሕጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የንግድ ሥራ ለመጀመር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የቡድን 20 አባል መሆኑ በዓለም አቀፍ መድረክ የአሕጉሪቷን ጥቅሞች ለማስከበር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ኢትዮጵያ እንደምታምን ዶ/ር ጌዲዮን መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።