AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደኀንነት መጠበቅ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለነባር ዲፕሎማቶች እና ለወጣት በጎ ፈቃደኛ ካዴቶች ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በስልጠናው ዙሪያም አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደኀንነት በተመለከተ የኢትዮጵያን ሚና አስመልክተው ገለፃ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናው አስተማማኝ ሰላም እና ደኀንነት እንዲጠበቅ እንዲሁም የተረጋጋ እንዲሆን ከሌሎች አገራት ጋር ጉርብትናን በማጠናከር በትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በመርህ ላይ በመመስረት በኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት መስኮች እንዲጠናከሩ በጋራ መስራት እንደሚገባ አንስገንዝበዋል።
የአገርን ብሔራዊ ጥቅም በተሟላ ሁኔታ ለማስከበር እና የሕዝብን አደራ ለመወጣት በመጭው የካቲት ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ዲፕሎማቶች እና ወጣት በጎ ፈቃደኛ ካዴቶች በአገራዊ ፍቅር ስሜት ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።