AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል ነፀብራቅ መሆንዋን የታሪክ እና ባህል ምሁርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በአድዋ ድል አማካኝነት በአፍሪካ የነበረውን የቅኝ ግዛት ስርዓት ለማፈራረስ ትልቅ ድርሻ እንደተወጣች ፕሮፌሰሩ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ሀገር መሆንዋን የገለጹት ፕሮፌሰር አህመድ፣ በዚህም አፍሪካን በመወከል አይነት ስሜት ስለ አፍሪካ ሀገራት ነፃነት ታንፀባርቅ ነበር ብለዋል፡፡
ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ቢሆን በፋሽስት ጣሊያን ጊዜ ሁሉም አፍሪካዊያን በቅኝ ግዛት ስር ቢሆኑም እንኳ የኢትዮጵያን ትግል ይደግፋ እንደነበር ያመላከቱት ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ለአፍሪካዊያን ነፃነት ትታገል ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም መስራችና ባለቤት ሆና ለዲፕሎማቲክ ማዕከልነት የተመረጠችበት ምክንያትም ለአፍሪካዊያን በነበራት አበርክቶ እንደነበር ነው ፕሮፌሰሩ የገለጹት፡፡
በወቅቱ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ለመውጣት ትግል ለሚያደርጉ ታጋዮች ኢትዮጵያ ድጋፍ ስታደርግ እንደነበርም አመላክተዋል፡፡
ከነፃነት በኋላም ከወሰን ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ግጭቶች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የነፃነት ጠባቂ ሆና መቆሟን የገለጹት ፕሮፌሰር አህመድ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላም መስፈን ትልቅ ሚና መጫወቷን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሱዳን፣ በዩጋንዳ እና በሩዋንዳ ለሰላም ለማስጠበቅ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ለዚህ ማሳያዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፣አዲስ አበባ አሁን ላይ የአፍሪካ እምብርት ሆና ደምቃ የምትታየው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ባበረከተቻቸው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦዎች በመመረጧ ነው ብለዋል፡፡
ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም፣ ልማት እና እድገት ይበጃሉ የምትላቸውን ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳዮች በአጀንዳነት ልታቀርብ እንደምትችል ፕሮፌሰሩ አመላክተዋል፡፡
በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ እና በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነት፣ ስለ ሰላም፣ በምግብ ራስን ለመቻልና ግብርናን ለማዘመን ስለሚካሄዱ ተግባራት፣ ስለ አጀንዳ 2063 አተገባበር፣ የአፍሪካ ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ለማብቃት መሰራት ስለሚገባቸው ስራዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ስለተጀመረው እና ለሌሎች ሀገራት ከተሞች ልምድ ሊወሰድበት ስለሚችለው የኮሪደር ልማት እና ሌሎች አካላት በሚያቀርቧቸው ሀሳቦች ዙሪያ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት ሊደረግባቸው እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ፕሮፌሰር አህመድ ገልጸዋል፡፡
በአስማረ መኮንን