ኢትዮጵያ በ92ኛው የኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው

AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በስኮትላንድ ግላስኮው እየተካሄደ በሚገኘው 92ኛው የኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራውና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ እና የብሔራዊ ኢንተርፖል መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደጀኔ በቀለ ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የድርጅቱ አባል ሀገራት የፖሊስ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የተለያዩ ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታመር የድርጅቱ አባል ሀገራት ለዓለም ሰላም መስፈን በትብብር በመስራት እያደረጉ ያሉትን ጥረት አድንቀው ሀገራቸው ለኢንተርፖል እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንምትቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጀነራል ከኢንተርፖል ኃላፊዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ የድርጅቱን ዓመታዊ ጉባዔ እንድታዘጋጅ ጥያቄ አቅርበዋል።

የድርጅቱ ኃላፊዎችም በቀጣይ ዓመታት የሚከናወኑ የኢንተርፖል ጉባኤዎች ለአፍሪካ ወይም የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ እንደሚያመቻቹ መግለጻቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ልዑክ ቡድኑ ፖሊስ የሚገለገልባቸው ቁሳቁሶች እና ፖሊስ የሚጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂ አምራች ከሆኑ እና ምርታቸውን በጉባኤው ላይ ካቀረቡ ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርጓል።

በዓመታዊው ጠቅላላ ጉባኤ ያለፈው ዓመት የድርጅቱ ሥራ አፈጻጸም እንዲሁም በቀጣይ እቅዶች እና የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጎ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።

ልዑኩ በቀጣይ ቀናት ከስብሰባው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review