AMN-የካቲት 13/2017 ዓ.ም
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ ዛሬ በተጀመረዉ የቡድን 20 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በስብሰባው ላይ ዶ/ር ጌዲዮን ባደረጉት ንግግር ዓለማችን የጂኦ-ፖለቲካ ፉክክር፣ ግጭት እና የአየር ንብረት ለዉጥን የመሳሰሉ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች መሆኑን ጠቁመዉ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የቡድን 20 አባል ሀገራት ወሳኝ ሚና እንደሚጠበቅባቸዉ ገልጸዋል ።

ኢትዮጵያ የታዳጊ ሀገሮች በተለይም የአፍሪካዉያን የመልማት ጥረት ድጋፍ እንዲያገኝ፣ የዓለም አቀፍ ስርዓት ፍትሃዊ እንዲሆን እና ዓለማችን የገጠሟት ፈተናዎች መፍትሄ እንዲያገኙ ከቡድን 20 አባል ሀገራትና ከዓመቱ ሊቀመንበር ደቡብ አፍሪካ ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከተቋቋመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር እየተካሄደ በሚገኘዉ የቡድን 20 አባል ሀገራት የ2025 ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች የምትገኘዉ በዓመቱ ሊቀመንበር በሆነችዉ ደቡብ አፍሪካ በቀረበላት ግብዣ ነው።
ስብሰባው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የዘላቂ ልማት ግቦች ፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የታዳሽ ኢነርጂ ልማት እና የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።