ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሕዝብ ለሕዝብ፣ በቴክኖሎጂ እና አቅም ግንባታ፣ ቱሪዝም እንዲሁም በሌሎችም የልማት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማሳደግ የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

የመጀመሪያው የኢትዮ – ታንዛኒያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተመራው ምክክሩ በኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ መካከል የዳበረ የሁለትዮሽ ትብብር መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።

የታንዛኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር መሐሙድ ታቢት ኮምቦ ሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የረዥም ዘመን የሁለትዮሽ እና ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥር ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ፣ የዓባይ ተፋሰስ ኢኒሸቲቭ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ቀጠናዊ እና አህጉራዊ ትብብሮችን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ አብረው የሚሰሩባቸው በርካታ ዘርፎች እንዳሉም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችሉ የልማት ሥራዎች ላይ ያላቸውን ትብብር ሊያጠናክሩ ይገባልም ብለዋል።

መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ግብርና፣ መሠረተ ልማት፣ ኃይል፣ አምራች ዘርፍ፣ ቱሪዝም እና ባህል፣ አቪየሽን፣ ቴክኖሎጂ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የዜጎች ነፃ ዝውውር እና በመሳሰሉ ዘርፎች ሀገራቸው ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት የምታጠናክርባቸውን የትብብር ዘርፎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዘርዝረዋል።

በዚህ ረገድ ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ለምትመሰርተው ጠንካራ የልማት ትብብር ስኬት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) ሁለቱ ሀገራት በፈተናም በስኬትም ዘመናት በጥብቅ ወዳጅነት የፀና ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ስለመሆናቸው አንስተዋል።

ከ1964 እ.አ.አ የሚጀምረው ይፋዊ የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተቋማዊና ሀገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ ወደ ሚያስችል ምዕራፍ ማላቅ ይገባል ብለዋል።

ከልማት እና ዕድገት ዘርፎች ባለፈ በቀጠናዊ ደኅንነት ዙሪያ ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ በጎ ሚና መወጣት እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

በሀገራቱ መካከል የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን በ2017 የተመሰረተ የትብብር ማጠናከሪያ ማዕቀፍ ነው።

የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን የሁለቱን አገራት ግንኙነት የጠበቀ ትብብር እንዲኖር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአቡ ቻሌ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review