ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደረሱ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደረሱ

AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም

ሁለተኛው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገርና በአዲስ አበባ የሚገኙ 21 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ውይይቱ የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተገልጿል።

በውይይቱ ማጠናቀቂያ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

ተወካዮቹ ሽብርተኝነትን መዋጋት ጨምሮ ቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና መልሶ ግንባታ፣ ኢኮኖሚ፣ ልማት፣ ፋይናንስ፣ ንግድ እና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የባለ ብዙ ወገን ማዕቀፍ ትብብር ውይይት የተደረገባቸው አጀንዳዎች ናቸው።

በውይይቱ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን እና የሀሳብ ልውውጦችን የሚያጠናክሩ ጥረቶችን ለማድረግ መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት ስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ እ.አ.አ በ2023 መካሄዱ ይታወቃል፡፡

የአጋርነት መድረኩ መካሄድ የጀመረው ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የሳሞአ ስምምነትን ከፈረሙ በኋላ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት በራሱ ማዕቀፍ እና የኅብረቱ አባል አገራት ከኢትዮጵያ ጋር በፈረሟቸው ስምምነቶች አማካኝነት ሀገሪቷ የፋይናንስ ድጋፎችን እያገኘች እንደምትገኝ መግለጫው አትቷል።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2016 የስትራቴጂክ አጋርነት ትብብር መፈራረማቸው ይታወቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review