AMN- ህዳር 9/2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢኖንሴባ ሎሲን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ላይ የመከሩ ሲሆን፤ የሁለቱን ሀገራት የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከርም እንደሚገባ በውይይቱ አንስተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በንግድ፣ ቱሪዝም እና በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እየተካሄደ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይታቸው ሁለቱ ሀገሮች በአፍሪካ ህብረት፣ በብሪክስ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እና እድሎችን ለመጠቀም ትብብርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተወያይተዋል።
አምባሳደር ኢኖንሴባ ሎሲ በሥራ ዘመናቸው በግብርና፣ ንግድ፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ላይ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ልውውጥ በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ሁለገብ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናዊ እና አለም አቀፋዊ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ እያደረገች ያለውን ወሳኝ ሚና አድንቀው፤ በዚህ ረገድ መንግስታቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።