ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሕማማትን ተሻግራ ወደ መንሰራራት እየገሰገሰች ትገኛለች ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የአገልግሎቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤዉ አደረሳችሁ!
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር፣ መረዳዳትና መተሳሰብ በላቀ ደረጃ የሚስተዋልበት ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ምዕመናን በዐቢይ ጾም ሲያከናውኗቸው የነበሩ በጎ ተግባራትን በትንሣኤ በዓልና ከዚያም በኋላ አጠናክረው በማስቀጠል አርዓያ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ትንሣኤ ከሕማማት እና ስቅለት ቀጥሎ በፅናት እና በመሥዋዕትነት በማለፍ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ሕማማትን ተሻግራ ወደ መንሰራራት እየገሰገሰች ትገኛለች፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ውድ ዋጋ ከፍለው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብረው እንዳስረከቡን፣ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የልማት ውጥኖቿን እያሳኩ ወደ ከፍታዋ እያወጧት ትገኛለች፡፡ በዚህ የድልና ስኬት ጓዳና ላይ ባለንበት ወቅት በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የድል፣ የተስፋና መዳን ምክንያት ተደርጎ የሚቈጠረዉን የትንሣኤ በዓል በታላቅ ድምቀትና መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዓሉን እንደተለመደዉ በመረዳዳት፣ በመተሳሰብና ዐቅመ ደካሞችን በማገዝ እና ማዕድ በማጋራት ማክበር ከሃይማኖቱ ተከታዮች የሚጠበቅ ነው፡፡
በድጋሜ ለመላዉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤዉ በሰላም አደረሳችሁ!