ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ መተካት የሚያስችሉ ፋብሪካዎች በዚህ ዓመት ወደ ምርት ይገባሉ – ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ መተካት የሚያስችሉ ፋብሪካዎች በዚህ ዓመት ወደ ምርት ይገባሉ – ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ

AMN-ጥር 16/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚያስችሉ ፋብሪካዎች በተያዘው ዓመት ተጠናቀው ሥራ እንደሚጀምሩ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የተገነባውን የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካን መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የታጠበ የድንጋይ ከሰል ከውጪ ስታስገባ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀውን ፋብሪካ ጨምሮ በዚህ ዓመት ተጠናቀው ወደ ስራ የሚገቡ አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከውጭ የሚገባውን ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካትና የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።

ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም መስራት ሲጀምሩ በዓመት ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በተጨማሪ እስከ 400 ሺህ ቶን ትርፍ ማምረት እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ ተመርቆ ስራ የጀመረው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ በዓመት 450 ሺህ ቶን ያለቀለትና ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል ማምረት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

ይህም የሀገሪቱን 25 በመቶ የድንጋይ ከሰልን ፍላጎት እንደሚሸፍንም ነው የጠቆሙት፡፡

ፋብሪካው ለግብዓት የሚሆን ጥሬ የድንጋይ ከሰል ከሚያቀርቡ አምራቾች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡

የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ በፍቃዱ አሠፋ በበኩላቸው ፋብሪካው ጥራቱን የጠበቀ የድንጋይ ከሰል ምርትን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንደሚያቀርብ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፋብሪካው በዓመት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል የመፍጨት አቅም እንዲኖረው የሚያስችል ማስፋፊያ እንደሚደረግለትም ጠቁመዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review