
AMN- ህዳር 9/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር (ፒ4ጂ) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ መመረጧ ተገለጸ።
ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ትብብር (ፒ4ጂ) በፈረንጆቹ 2017 የተመሰረተ ሲሆን፤ ዴንማርክ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ሜክሲኮ እና ቬትናም መንግሥታት የተመሰረተ አጋርነት ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ሮቢን ማክጉኪን ጋር መክረዋል፡፡
በአዘርባጃን ባኩ እየተካሄደ ካለው የኮፕ 29 ዓለም አቀፍ ጉባዔ ጎን ለጎን የተካሄደው የስራ ኃላፊዎቹ ውይይት የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግሉ ዘርፍ በሚያበረክተው በጎ ሚና ዙሪያ ማተኮሩ ተገልጿል።
ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር (ፒ4ጂ) እያደረገ ላለው ተሳትፎም ሚኒስትር ዴዔታው አመስግነዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የአየር ንብረት ተፅዕኖ ለመከላከል ድጋፍ ለማድረግ በሀገራት መካከል ትብብር እንዲጎለብት የማድረግ ተልዕኮ ያለው የአረንጓዴ ልማት ትብብር (ፒ4ጂ) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ኢትዮጵያ መመረጧም ተመለክቷል።
ውሳኔው ኢትዮጵያ በዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲጎለብት እየተወጣች ላለው ጉልህ ሚና ዕውቅና የሰጠ ሆኗል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ሮቢን ማክጉኪን ጋር ባደረጉት ምክክር፤ በዘላቂ የልማት ዕቅዶች ውስጥ የጅምር ፈጠራ ሀሳቦች ሚናን ማላቅ እንዲሁም ለአካታች የኢኮኖሚ ሽግግር ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያም መክረዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረግ ዓለም አቀፍ ጥረት የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም ሚኒስትር ዴዔታው ማረጋገጣቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።