
AMN – ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን በማረጋገጥ ረሀብን ለማጥፋትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለዚህም አስቻይ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየሰራች መሆኗን የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ከረሀብ ነጻ አለምን ለመፍጠር የሀገራት መሪዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታችዉ ተቋማት ሃላፊዎች በአዲስ አበባ እየመከሩ ነዉ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ሪፎርሞች ምርታማነትን ለማሳደግ እና ለዚህም አስቻይ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየሰራች ስለመሆኑ ተናግረዋል ፡፡
ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት እና በዘርፉ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማላቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ተፈጥሮን የመንከባከብ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ ቀልጣፋ አሰራሮችን የመተግበር ስራን በትጋት እየሰራች ስለመሆኗ ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮችና መሰል ተቋማት በተሰሩ ስራዎች በርካታ ለዉጦች ስለመመዝገባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ተናግረዋል ፡፡
ረሃብ በአንድ ቦታ ብቻ የተገደበ አይደለም በዚህም የጋራ ምክክር እና ርምጃን ይጠይቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም በሁለንተናዊ መልኩ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እዉቀትን መለዋወጥ ቴክኖሎጂን በምርቶች መተግበር እና መንግስታት በትበብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርና ዘርፉን ለማዘምን በቴክኖሎጅ መላቅ ላይ ሰፊ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
መንግስታት እና ተቋማት በጋራ በመስራት በዚህም የታሰበዉን ረሀብን የማጥፋት አላማ ዕውን ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደው ከረሃብ ነጻ ዓለም ኮንፈረንስ እንዲሳካ ለሰሩ እና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል ፡፡
በተመስገን ይመር