ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ናት – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ናት – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

AMN ሚያዚያ 18/2017

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን እስከ እ.አ.አ ማርች 2026 ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ እንደሆነች የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።

በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ ግሩፕ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ እና ኡዝቤኪስታን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደትን የተመለከተ የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ተካሄዷል።

ውይይቱ የተዘጋጀው በዓለም ባንክ ግሩፕ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ ትብብር ነው።

በመድረኩ ላይ የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ፣ የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ንድያሜ ዲዮፕ እና የአይኤምኤፍ የስትራቴጂ ምክትል ዳይሬክተር ኬን ካንግ ተሳትፈዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት እና ማዕቀፉ ለኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ያለውን አንድምታ አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ እ.አ.አ ማርች 2026 በካሜሮን ያውንዴ በሚካሄደው 14ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ አባል የመሆኗን ሂደት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጸዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ የኢትዮጵያ እና ኡዝቤኪስታን የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደት እንዲፋጠን የባለብዝሃ ወገን ተቋማት እና የሁለትዮሽ አጋሮች አስፈላጊውን የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ህግን መሰረት ባደረገው የዓለም የንግድ ስርዓት አካል ለመሆን ያሳየችውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ለኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review