AMN ታሕሣሥ 6/2017 ዓ .ም
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልዕልናዋን ለማረጋገጥ የግብርና ልማትን፣ ኢንዱስትሪን፣ ማዕድንን፣ ቱሪዝም እና ዲጅታል ኢኮኖሚን ዋነኛው የትኩረት መስክ እና የኢኮኖሚዋ ምሳሶች በማድረግ ፈጣን የተባለውን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ነው ብለዋል ።
ይህን እውነታ እኛ ባለቤቶቹ ከምንናገረው በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማት በገሃድ እየተናገሩ፣ እየጻፉና ለታሪክ ዶክመንት እያደረጉ ይገኛል ብለዋል።
ለምሳሌ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሆነው አይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2024 በጠቅላላ ሃገር ውስጥ ምርት ኢትዮጵያን ከአምስቱ የአፍሪካ ምርጦች ውስጥ አንዷ እንደሆነች በሪፖርቱ ይፋ ማድረጉን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ለዚህ ስኬታማ ድል የበቃችው ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመከተል፣ ለየኢኮኖሚ ዘርፎቹ የተስተካከለ አቅጣጫና ስትራቴጂ በማስቀመጥ እና በብቃት መተግበር በመቻሏ ነው።
በግብርናው ዘርፍ በመኸር አዝመራ፣ በበጋ መስኖ እና በበልግ አዝመራ ስንዴን ጨምሮ ለአምስት ዋና ዋና ሰብሎች የተለየ ትኩረት በመስጠት ምርታማነትን በጥራትና በመጠን በትጋት ጨምራለችም ነው ያሉት ዶክተር ለገሰ ።
በበጋና በክረምት በአትክልትና ፍራፍሬ በተለይም ለሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፤ ለቡና፣ አኩሪ አተር፣ ቦሎቄ፣ ሰሊጥ፤ በሌማት ትሩፋት እና የአርንጓዴ አሻራ ፕሮግራሞችን ቀርጻ በውጤታማነት ተግብራለች።
ዶ/ር ለገሰ በአርባ ምንጭ እና አካባቢው በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በምስራቅ ጉጅ በወርቅ ልማት፣ በምዕራብ ጉጅ በዘመናዊ የቡና ልማት፣ በሀዋሳ የኮሪደር ልማት እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ከፍ ያለ የልዕልና መንገድ መጀመሩን ተመልክቻለሁ ብለዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቤንች ሸኮ የሁለት ወረዳዎች (ደቡብና ሰሜን ቤንች) እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የዳኝነት ዋና መቀመጫ፣ እና የቤንቺ ሸኮ መዲና በሆነችሁ ሚዛን አማን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችንም መመልከታቸውን ጠቁመዋል ።
በነዚህ አካባቢዎች ያሉትን ፀጋዎች ለመግለጥና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ለሌሎች አካባቢዎች ትምህርት የሚሰጡ እና የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞን ትክክለኛነት የሚያንፀባርቁ ናቸው።
ለሌሎች ዘርፎችም እንዲሁ ከሀገራችን እና ከዘርፎች ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ ፕሮግራሞች በመንደፍ በተገቢው መንገድ በመተግበር ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል በመልእክታቸው።