AMN ጥር 11/2017 ዓ.ም
በሀገራችን ያሉ እንደ ጥምቀት ያሉ የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም መስህቦችም ጭምር በመሆናቸው ልንጠብቃቸው እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ አስገነዘቡ፡፡
የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በጃንሜዳ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡
በበአሉ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ባስተላለፉት መልእክት ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ሀይማኖታዊ በዓላት ፣ ባህልና እሴቶች በጋራ የሚከበሩባት ድንቅ ሀገር ናት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠብቃ ያቆየችውና በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል የእዳ ደብዳቤያችን የተደመሰሰበት በዓል እንደመሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በመውሰድ እርስ በርስ ልንፋቀርና ልንደጋገፍ ይገባል ብለዋል ፡፡
እንደነዚህ ዓይነት በዓላት እና ባህሎቻችን ለዘመናት ሳይደበዝዙ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ መቆየታቸውን አውስተዋል ፡፡
እነዚህ በዓላት እና ባህሎች የቱሪዝም መስህቦቻችን በመሆናቸው ልንጠብቃቸው ይገባልም ብለዋል፡፡
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴርም ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶቻችን ተጠብቀው እንዲቆዩና የቅርሶችም ደህንነት እንዲጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል ፡፡
በሽመልስ ታደሰ