እንግልትን የረታው ቴክኖሎጂ

•  አገልግሎቱ ዲጂታላይዝድ መሆኑ እንግልት መቀነሱን ተገልይጋዮች ተናገሩ

አዲስ አበባ ከምትፈተንባቸው ጉዳዮች መካከል ኋላ ቀር የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ ይህ ክፍተት ነዋሪዎችን ለእንግልት፣ የገንዘብ ወጪና የጊዜ ብክነት ሲዳርግ፣ በከተማዋ ስምና ዝና ላይም ጥላሸት ሲያኖር ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታላይዝ ለማሸጋገር ሲደረግ በቆየ ጥረት አበረታች ውጤቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ በተለይ በከተማዋ የመሬት ልማትና አስተዳደር፣ በጤና ተቋማት እና በሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ተግብራት ላይ ጉልህ መሻሻል ታይቷል፤ ተገልጋዮችም ይህንኑ ይናገራሉ፡፡

በከተማዋ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ውጤት ካስገኘባቸው ተቋማት መካከል የከተማዋ መሬት ልማትና አስተዳደር አንዱ ነው፡፡ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ተገኝቶ የተገልጋዮችን አስተያየት ሰብስቧል፡፡ ዘርፉን ከሚመሩ የስራ ኃላፊዎችም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የነበሩ ክፍተቶች አሁን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙና የወደፊት ውጥኖችን የተመለከቱ ማብራሪያዎችን በመጠየቅ በዚህ ፅሑፍ ያመላክታል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ባለሙያዎች የኦን ላይን አገልግሎት ምዝገባ ስራ ሲከውኑ

ወይዘሮ አማከለች ስዩም ከሁለት አስርት አመታት ላላነሰ ጊዜ ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው እንደነበር ያስታውሳሉ፤ በውጭ አገር በነበራቸው ቆይታም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ያለው አገልግሎት ቢሮክራሲ የበዛበት፣ አታካችና በሙስና የተተበተበ እንደሆነ ሲሰሙ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከውጭ አገር መጥተው ያዩት ግን ከሰሙት ጋር እምብዛም እንደማይገናኝ ተናግረዋል፡፡

“ወደ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የመጣሁት የጋራ ካርታን ወደ ግል በማዘዋወር የባለቤትነት መብቴን ለማረጋገጥ ነበር” የሚሉት ወይዘሮ አማከለች፣ “በዚሁ መሰረት በኦን ላይን አገልግሎት ባመለከትኩትና በተሰጠኝ ቀጠሮ መሰረት ከየትኛውም አገልጋይ ጋር ሳልገናኝ ሰንብቼ፣ አሁን ወረፋ እንደደረሰኝ የልኬት ባለሙያ ተመድቦልኝ ለማስለካት ችያለሁ” ብለዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ከለውጥ ስራዎች አኳያ ከቅርብ አመታት ወዲህ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲልም በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ የተለያዩ እቅጣጫዎች ቢቀመጡም በተለያዩ ምክንያቶች ችግሮቹን መፍታት ሳይቻል መቆየቱን ነው፡፡ በቅርቡ እንደከተማ አስተዳደር የዲጂታል አገልግሎትና የአውቶሜሽን ስራዎች እየዳበረ መሄድ ግን አዲስ የታሪካዊ ምዕራፍ እየገለጠ መምጣቱን ነው ተገልጋዮች የሚናገሩት፡፡

አቶ ድሪብሳ አራርሳ የተባሉ ተገልጋይም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ያነጋገርናቸው ሌላኛው ባለጉዳይ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ የባለቤትነት ማረጋጋጫ ካርታን ወደዲጂታል ለማስቀየር የኦንላይን ምዝገባና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መጀመሩን ባለማወቃቸው  በአካል ወደ ተቋሙ መጥተው ቢመዘገቡም በግል ስልካቸው በማግስቱ እንደሚስተናዱ ቀጠሮ ደርሷቸው አስፈላጊውን አገልግሎት ማግኘት ችለዋል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሊግዲ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ተገልጋይ የሚበዛባቸውና ከፍተኛ የስራ ጫና የሚፈጠርበት እንደሆነ አስታውሰው፣ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የኦን ላይን አገልግሎት ችግሩን ከማቃለሉም ሌላ የስራ ቅልጥፍና መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ በማብራሪያቸው፣ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ባለሙያዎችና ባለጉዳዮች ፊት ለፊት ይገናኛሉ። ይህም ለሙስና የሚያጋልጥ አካሄድ ነበረው፤ ባለሙያዎች የአሰራሩን ክፍተት በመጠቀም ሆን ብለው ፋይል የመደበቅና ከባለጉዳይ ጋር የመደራደር አዝማሚያ ያሳዩ ነበር ብለው፣ የአሁኑ አሰራር ግን ይህን ችግር ማስቀረቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ባለጉዳይ በኦን ላይን መመዝገብ ከመቻሉም ሌላ በቀጠሮው ቀን አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣም ከባለሙያ ጋር ንክኪ ሳይፈጥር በተዘረጋው ሲስተም መገልገል መቻሉ ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎ ማግኘት ማስቻሉን አቶ ሙሉጌታ አክለው ገልፀዋል፡፡

የኦን ላይን አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት በየቀኑ ከ500 የሚበልጡ ተገልጋዮች በአካል ወደ ተቋሙ በመምጣት ተሰልፈው ወረፋ ይጠብቁ እንደነበር ገልፀው፣ አሁን ላይ የሊዝ ውል ለመዋዋልና መሃንዲስ ለመውሰድ በቀጠሯቸው ቀን ከሚመጡ ጥቂት ሰዎች በስተቀር በአካል የሚመላለሱ ባለጉዳዮች ቁጥር ቀንሷልም ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን አገልግሎቱ በኦን ላይን የሚሰጥ ቢሆንም ለአቅመ ደካሞችና ቴክኖሎጂን በቀላሉ መጠቀም ለማይችሉ ሰዎች በተቋሙ የመረጃ ዴስክ በባለሙያዎች ድጋፍ አገልግሎቱ የሚሰጥበት ስርዓትም ተመቻችቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጂንሲ የለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የኦን ላይን አገልግሎት አለመጀመሩ የስራ ጫናና የተገልጋይ እንግልት መፍጠሩን አቶ ኡርጌቻ ከፈኔ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጂንሲ የለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡርጌቻ ከፈኔ ጉዳዩን ሲያብራሩ፣ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በቅርብ የተመሰረተ ነው፡፡ ተቋማቱ በተለያዩ ህንፃዎች ተበታትነው ይገኛሉ፡፡ በተለይ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጂንሲ የለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሲስተም አልተዘረጋለትም፤ በመሆኑ ጊዜያዊ ችግሩን ለማቃለል ሲባል አገልግሎቱ የሚሰጠው ባለይዞታዎቹ በግንባር ቀርበው መመዝገብ ሲችሉ ነው ብለዋል፡፡

ለወደፊቱ ግን የኦን ላይን አገልግሎት ለመስጠት በዕቅድ ደረጃ መያዙን አስታውሰው፣ ለዚህም ስርዓቱን ለመዘርጋ በጨረታ ሂደር ላይ እንደሚገኝም ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

በዋናነት የመሬት ይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ስራዎችን የሚሰራ ቢሆንም ይህን መነሻ በማድግ ይዞታ መክፈል፣ መቀላቀል፣ የስም ዝውውር፣ ድጅታል ካርታ መስጠትና ማረጋገጥ፣ እዳ እገዳ፣ እዳ ስረዛን ጨምሮ ወደ 25 የሚጠጉ አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ክፍለ ከተማው በቅርቡ የተመሰረተ በመሆኑ አሁን ላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና የሪል ስቴቶች አገልግሎቶች በኦን ላይ እየተሰጠ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቴክኖሎጂና የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ቢቂላ፣ “በከተማዋ አጠቃላይ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘመናዊ፣ በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ በመፍታት ስር ነቀል የሆነ የሪፎርም ስራ ለመስራት ተከታታይና ብርቱ ስራ ሲከናወን ቆይቷል” ይላሉ፡፡

በተቋሙ በይዞታና መሬት ነክ ጉዳዮች ወደ 40 የሚጠጉ አገልግሎቶች የሚሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 30 አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል አገልግሎት መግባት ችለዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሌሎችንም ወደ ስርዓቱ በሁሉም መዋቅሮች ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የምንሰጣቸውን አገልግሎቶች ወደ ስራ ለማስገባት በሪፎርሙ፣ በቴክኖልጂ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በተቋማት ኔትዎርኪንግ፣ በመሬት አገልግሎት ሲስተም ልማት፣ የመሬት መረጃዎችን ማደራጀት ወይም በመረጃ ድጂታላይዜሽንና አስተዳደር ሥርዓት፣ በቅንጅታዊ አስራር፣ ምቹ የስራ አከባቢ በመሰፍጠር፣ በተቋም አደረጃጀት እና ህጎች ማሻሻል ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡

እንደ አቶ ዘሪሁን ገለፃ፣ በከተማ ደረጃ የመሬት ህጎችን ሙሉ በሙሉ የማሻሻል እና የመሰብሰብ ስራ ከመሰራቱም ሌላ፣ መመሪያዎችን ማሻሻል ብሎም ተበታትኖ የነበረውን የመሬት መመሪያዎች ወደ አንድ ቋት የማስገባትና የአገልግሎት አሰጣጥ ማንዋሎች ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡

የቴክኖሎጂ መሰረት ልማት ዝርጋታ እና ሲስተም ልማት ስራ መሰራቱ፣ ማዕከልና ክፍለ ከተሞች በወረዳኔት መተሳሰራቸው፣ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ የሚችል ሲስተም መዘርጋት አስችሏል ያሉት አቶ ዘሪሁን፣  ለተገልጋዩም ሆነ ለሰራተኛው ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠር፣ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት መርህ ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ መጀመሩ የሪፎርሙ ተስፋ ተደርጎ ይወሰዳልም ብለዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን የመረጃ አያያዝና አስተዳደር ስረዓቱን የማሻሻል፣ የፋይል ዲጅታይዜሸን ስፔሻል መረጃ ማደራጀት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቅንጅታዊ አሰራሮች ከአዲስ አበባ እና የፌዴራል ገቢዎች፣ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት፣ ፋይዳ መታወቂያን ጨምሮ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር ማስቻሉንም በስኬት ያነሳሉ፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review