እየተካሄደ ባለው የመንገድ ላይ ክትትል እና ድጋፍ በአሽከርካሪዎች እና በተሽከርካሪዎች ላይ በርከታ ጉድለቶች መታየታቸው ተገለፀ

You are currently viewing እየተካሄደ ባለው የመንገድ ላይ ክትትል እና ድጋፍ በአሽከርካሪዎች እና በተሽከርካሪዎች ላይ በርከታ ጉድለቶች መታየታቸው ተገለፀ

AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም

ለዘጠኝ ቀናት በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ በተለያዩ መንገዶች እየተካሄደ ባለው የመንገድ ላይ ክትትል አና ድጋፍ በአሽከርካሪዎች እና በተሽከርካሪዎች ላይ በርከታ ጉድለቶች መታየታቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ገልፀዋል።

ከተለያዩ ባለድረሻ አካላት ጋር እየተካሄደ ባለው ክትትል እና ድጋፍ ላይ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ሁኔታ ሳያሟሉ ቦሎ ያላቸው ተሽከርካሪዎች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡

እንደ ሀገር ወጥ የሆነ ታሪፍ ቢኖርም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ መኖራቸው፤ ተሽከርካሪው ከመጫን አቅሙ በላይ ትርፍ ጭነት የሚጭኑ እንዲሁም በአንዳንድ አሽከርካሪዎች ተደራራቢ የትራፊክ ቅጣት ያላቸው በመሆኑ በህግ አካላት አስፈላጊው የምክር እና የእርምት እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

በሀገራችን ከመንገድ ትራፊክ አደጋ ጋር ተያይዞ በሰው ህይወት እና በኢኮኖሚ የሚደርሰውን ጉዳት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ እንዲቻል የክትትል አና ድጋፍ ስራው ላይ አሽከርካሪዎች አስፈላጊውን የመንገድ ደህንነት ጥንቃቄና ስነ-ምግባር ተላብሰው የራሳቸውን እና የተሳፋሪውን ደህንነት ጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ የተመከሩ መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል።

በቀጣይ የሚታዩ ቸግሮችን ለመቅረፍ፣ የተሽከርካሪ መርማሪ ተቋማትም ሆኑ የአሽከርካሪ ማስልጠኛ ተቋማት ከተለመደው አሰራር ውጭ በቴክኖሎጂ በተደገፈ እና በዲጂታል ሲስተም ከማዕከል ቁጥጥር ለማድረግ እንዲቻል ዘላቂነት ያላቸው ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ብሄራዊ መለኪያን የጠበቁ ሞዴል ማሰልጠኛ እና ምርመራ ተቋማት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review