
የእግር ኳስ ስፖርት ከውድድር ባለፈ ለአእምሮና ጤና ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ ማህበራዊ ትስስርን በማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማፋጠንንና በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም እ.ኤ.አ. በ2024 ጠቅላላ ጉባኤው የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ቀን እንዲሆን ያወጀውም ለዚሁ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በዓለም ላይ በጣም ተወዳጅ የሆነውን ስፖርት እንዲያከብሩ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በየዓመቱ ግንቦት 17 ቀን የዓለም እግር ኳስ ቀን ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል። በተጨማሪም ዕለቱም በታሪክ የመጀመርያው የሆነውና በ1924 በፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ በተካሄደው ሁሉም አህጉሮች የተሳተፉበትን የበጋ ኦሎምፒክ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድር 100ኛ ዓመትን ለማሰብና ለዚህ ትልቅ ምዕራፍ እውቅና ለመስጠት መሆኑ ተገልጿል።
ሀሣቡን ለጉባዔው ያስተዋወቁት በሊቢያ የተመድ አምባሳደር ታሄር ኤል-ሶኒ በወቅቱ ለጉባኤው እንደተናገሩት እግር ኳስ በዓለም ዙሪያ የሚዘወተር እና ብዙ ተከታይ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደሩ እግር ኳስ በሁሉም የእድሜ ክልሎች ያሉ በሙሉ በመንገዶች፣ በመንደሮች እና በትምህርት ቤቶች ለመዝናናት እና ለውድድር ከሚያካሂዷቸው ጨዋታዎች ሁሉ ተወዳጅ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ሁሉ እግር ኳስም በዓለም ዙሪያ ሰላምና አንድነትን ለመገንባት መሳሪያ መሆኑን ጠቁመዋል። አያይዘውም ቀኑን ማሰብ ያስፈለገው በዓለም ላይ እጅግ ተወዳጅ የሆነውን የእግር ኳስ ስፖርት ደጋፊዎች እንዲያከብሩት ለማስቻል ነው ተብሏል። ውሳኔው ሁሉም ሀገራት እግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርቶችን እንዲደግፉ በማበረታታት ሰላምን፣ ልማትን እና የሴቶችና ልጃገረዶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያግዛል መባሉን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
የእግር ኳስ ስፖርት ኃያልና ጉልህ ሚናውን ከሚጫወትባቸው መስኮች አንዱ በሰላም ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሙ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ባላንጣዎችን የማገናኘት፣ ጦር የተማዘዙ ሀገሮችን በስፖርት መድረክ እኩል የመዳኘት ዕድሉ በዓለም አደባባይ የታየበት ማኅበራዊ ዘርፍ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ስፖርት ሃብታም፣ ደሃ፣ ዘር፣ ቀለም፣ ኃይማኖት ሳይለይ ለሰው ልጆች በእኩልነት የሚሰራና ሰዎችን በቀላሉ የሚያሰባስብ ስለመሆኑም ብዙ ክስተቶችን በአስረጅነት መጠቀስ ይቻላል።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1914 በአንደኛው የዓለም ጦርነት የገና በዓል ማግስት የተፈጠረውን የታሪክ አጋጣሚ እዚህ ጋር እንጥቀስ፡፡ የገና በዓል ማግስት ምሽት የእንግሊዝና የጀርመን ወታደሮች በቤልጂየም ተራራማ ቦታዎች ምሽጋቸውን ይዘው ተፋጠዋል። በገና በዓል ሳቢያ የተዘመሩ ዜማዎች፣ ቤተሰብን የሚያስታውሱ፣ ምስጋና የበዛባቸው የዝማሬ ድምፆች መሰማት ጀመሩ፡፡ እነዚህም ዜማዎች ወታደሮችን ልብ አራርተው በወታደሮች መካከል ለምክክር ዕድል ተፈጠረ፡፡ የጥይት ድምጾች ለጊዜውም ቢሆን መሰማታቸው ቆመ፡፡
ቀጥሎም በሁለቱም ሀገራት ወታደሮች መካከል ለጊዜውም ቢሆን ውጊያውን እናቁም መልዕክቶች ተሰራጩ፡፡ በዛ በካቡዱና በመቶ ሺዎች ባለቁበት በአንደኛው የዓለም ጦርነት መሀል የሁለቱም ወገኖች ወታደሮች መሳሪያቸውን አስቀምጠው በማግስቱ እግር ኳስ ተጫወቱ። ከጨዋታው በኋላም ወታዶሮች እንዲሁ ዝም ብለው አልተለያዩም ነበር፡፡ ስፖርቱ የፈጠረላቸውን በጎ ስሜት ተጠቅመው በጋራ ፎቶ ተነስተዋል፣ የሞቱባቸውን ቀብረዋል፣ ቁስለኞችን አክመዋል፣ ስጦታ ተለዋውጠው ተለያይተዋል፡፡
ስፖርት ይህን ያህል ስልጣን አለው፡፡ በሰላም ግንባታና አንድነትን በማምጣት ሂደት ውስጥ እግር ኳስ ቁልፍ ሚና አለው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኬንያ ያሉ ወጣቶችን ወደ እርቅ ለማምጣት፣ በቡሩንዲ እርቅን ለመደገፍ እና በፓኪስታን ውስጥ የተለያዩ የሰላም ፕሮጀክቶችን ለመርዳት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ እንደዚሁም በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር አይቮሪኮስት የሆነውን ደግሞ ከተመለከትን ሰላምን በማምጣትና በህዝቦች መካከል አንድነትን በማጠናከሩ ረገድ እግር ኳስ ምን ያህል ድርሻ እንዳለው አንረዳለን፡፡
የሎሳንጀለስ ኒውስ ጋዜጣ ጸሐፊ ኬቨን ባክስተር እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2014 የተጨዋቹን በጎ አድራጎት ስራዎች ባተተበት ጽሑፉ የስፖርቱ ዓለም ያለው ዋጋ እንዲሁ በገንዘብ ብቻ የሚተመን እንዳልሆነ ያስረዳል። ስፖርታዊ ክዋኔዎች በሰዎች መካከል ጥብቅ ግንኙነትና መተሳሰብ እንዲፈጠረ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑንም በመጥቀስ በሰዎች ላይ የሚፈጥረው በጎ ተጽዕኖም ቀላል አልመሆኑ ጭምር ጋዜጠኛው ያስረዳል፡፡ በጥቅሉ ከላይ የጠቀስናቸው አጋጣሚዎች የሚያሳዩት እውነት ስፖርታዊ ክዋኔዎች ያዘሉት ዓላማና የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ከሜዳ ውጪ የሚደርስ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡
የቢቢሲ ዘጋቢዊ ቢል ዊልሰን ከሶስት ዓመት በፊት የስነልቦና ባለሙያ ፕሮፌሰር ጄን ሻንግን አነጋግሮ ያስነበበው ጽሑፍ የእግር ኳስ ስፖርት ምን ያህል የማህበረሰብ ለውጥ ግልጋሎት ላይ ሊውል ይችላል በሚል ሀሳብ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ ባለሙያዋ በሰጡት አስተያየት መሰረት ታዋቂ ስፖርተኞች ተጽዕኗቸው ከስፖርቱ ሲሻገር የተሻለ ዝና እናገኛለን ወይም ጥቅም ይሰጠናል ብለው አሰበው ብቻም ሳይሆን እሳቸው እንደሚሉት የስነልቦና ደህንነት ወይም እርካታ ስለሚሰጣቸው እንደሆነ አረጋግጫለው ሲሉ ለቢቢስ አስረድተዋል፡፡
የእግር ኳስ ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት እና የእርስ በእርስ ግብይት ፣ ሰላም እና ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያለውን ተፅዕኖ በመገንዘብ የዓለም እግር ኳስ ቀንን መሰየም ማስፈለጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃዎች ያሳያሉ።
የተባበሩት መንግስታት በየዓመቱ ታስቦ እንዲውል የፈለገበት ሌላኛው ሃሳብ ሁሉም ሀገራት እግር ኳስን እና ሌሎች ስፖርቶችን እንዲደግፉ የሚያበረታታ መሳሪያ በመሆን ሰላምን፣ ልማትን እና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ነው። እንዲሁም ሀገሮች እግር ኳስን እና ሌሎች ስፖርቶችን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ለማስተዋወቅ ፖሊሲዎችን እና ፕሮግራሞችን እንዲያወጡ ያበረታታል።
ሁሉም አባል ሀገራት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አካዳሚዎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ እና የግሉ ሴክተሮች የዓለም እግር ኳስ ቀንን በሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እንዲያከብሩ እና በሁሉም የእግር ኳስ ጥቅሞች በትምህርት እና በህዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉም ይጋብዛል።
ከላይ ለማሳያነት ያነሳናቸው ጉዳዮች ስፓርት ጠንካራ ሀገራዊ ህብረትን፣ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን እና ሁለንተናዊ እድገትን ለማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን ነው። በተለይ የእግር ኳስ ስፖርት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ በሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖችን በማጠናከር ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያሳያል።
እውቁ ብራዚላዊው የእግር ኳስ ኮከብ በአንድ ወቅት ስለእግር ኳስ የተናገረውን ጠቅሰን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ የዩኔስኮ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የነበረው ፔሌ “እግር ኳስ ሰዎችን አንድ ላይ የምታሰባስብበት ስፖርት ነው፣ ሀብታም ብትሆን፣ ድሀ፣ ወይም ጥቁር፣ ነጭ ብትሆን ለውጥ የለውም። አንድ ሀገር ነው። ይህ የእግር ኳስ ውበት ነው።” ብሎ ነበር፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ