ለተሳለጠ ገቢ አሰባሰብ ስርዓት የተለያዩ ስራዎችን በስፋት ሲያከናውን መቆየቱን የገለጸው ቢሮው ከሳምንታት በኋላ ለሚጀምረው የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ወቅት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ስለመዘጋጀቱ የቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡
ግብር ከፋዩ ከቤቱ ሆኖ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ግብሩን የሚያውቅበትና በጊዜው ያለምንም መጉላላት እንዲከፍል የሚያስችል ስርዓት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል፡፡
በዚህም መሰረት መዲናዋ በአጠቃላይ ካሏት 450 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች ውስጥ 350 ሺህ ገደማውን የሚይዘው የደረጃ ሐ ግብር ከፋይ ግብሩን በቀላሉ የሚከፍልበት ስርዓት ስለመዘርጋቱ ተነግሯል፡፡
ከደረጃ ሐ ግብር ከፋይ በዓመት 20 ቢሊዮን ብር ገቢ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ ምንም እንኳን ከአጠቃላይ የከተማዋ ግብር ከፋይ አብላጫውን ቢወስድም የሚያስገኘው ገቢ ግን በንጽጽር አነስተኛ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
ይህም ሆኖ የሚጫወተው ሚና ግን ቀላል የሚባል አለመሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 350 ቢሊዮን ብር ሆኖ መጽደቁ ይታወቃል፡፡
የመዲናዋ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ግብር መሆኑን ያስታወሰው ቢሮው የግብር ከፋዩ በታማኝነት ግብሩን መክፈል አስፈላጊነትን አጽንዖት ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም ግብር ከፋዩ ወቅቱን ጠብቆ ግብሩን እንዲከፍልና ከቅጣት እንዲድን አሳስቧል፡፡
በመቅደስ ደምስ