“ሙዚየሙ ብዙ ቅርሶች የያዘ በመሆኑና በአንዴ ሁሉንም መረዳት ስለማልችል ከጓደኞቼ ጋር በመሆን በተለያዩ ጊዜያት እየመጣሁ የመጎብኘት ልምድ አለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም የሰው ዘርና የእንስሳት ቅሪተ አካል ተመልክቻለሁ። ጥንታዊ መመገቢያና መጠጫ ቁሳቁሶች፣ ስእሎችና ሌሎችንም ጎብኝቻለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ሙዚየም በከተማችን መኖሩ የውጭ ሃገር ጎብኚዎችን ለመሳብ ያስችላል” ስትል ታነሳለች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ስትጎበኝ ያገኘናት ወጣት ቅድስት በላይ፡፡
ወጣቷ ሙዚየሙ አሁን ላይ እድሳት እየተደረገለት መሆኑን በመግለፅ ረዥም ጊዜ የሆነው በመሆኑ መታደሱ ጥሩ ነው። በውስጡ የተለያዩ ቅርሶች ስላሉም እንዳይበላሹ ያደርጋል። ግቢውም ሳቢ እንዲሆን ለመስራት መታቀዱ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆን ያስችላል ብላለች፡፡
ሌላዋ ሙዚየሙን ሲጎበኙ ያገኘናቸው ከናይጄሪያ የመጡት ቱሪስት ሊስ ክላቬሪ ናቸው፡፡ “ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በማህበራዊ የትስስር ገፆች ላይ እመለከት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሙዚየሙን ለማየት የወሰንኩት። በተለይ የሰው ዘር ቅሪተ አካል የሆነችው ሉሲን ለማየት ጉጉት ስላደረብኝ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ። በሙዚየሙ ሉሲን አይቻለሁ። የተለያዩ የአርኪዮሎጂ ግኝቶችንና ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶችንም ጎብኝቻለሁ፡፡ ደስ ብሎኛል” ብለዋል።
“ሙዚየሙ መታደሱ የሚገባው ነው፡፡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ በብዛት እንዲመጡ ያስችላል፡፡ የህብረተሰቡን ጥንታዊ ባህል የሚያንፀባርቁ፣ ታሪኩንና ማንነቱን የሚገልፁ ቅርሶች በሙሉ ሳይጎዱ እድሳቱ መከናወኑ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡” ሲሉም ገልፀዋል ጎብኚዋ፡፡

ኢትዮጵያ ታይተው የማይጠገቡ፣ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ የቱሪዝም መስህቦች አሏት፡፡ ከነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ይጠቀሳል፡፡ ሙዚየሙ በ1936 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መፃህፍት ወመዘክር” በሚል ስያሜ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነበር የተመሰረተው። ሲመሰረት የብሔራዊ ባንክ የሰራተኞች ክበብ ውስጥ ነበር፡፡ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ራሱን ችሎ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም” በሚል ስያሜ አምስት ኪሎ ቅድስት ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አገልግሎቱን በመስጠት አሁንም ድረስ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አንጋፋው ሙዚየም በተለያዩ ጊዜያት የተወሰነ እድሳት ቢደረግለትም ሙዚየሙን በሚመጥን መልኩ ባለመሆኑ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ውስጣዊና ውጫዊ እድሳት እየተደረገለት መሆኑን በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ ጥገናና ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀፍታሙ አብርሃ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ ገልፀዋል፡፡
አቶ ሀፍታሙ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሙዚየሙ ውስጣዊና ውጫዊ እድሳት ነው እየተደረገለት ያለው፡፡ የውስጣዊ እድሳቱ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ድጋፍ እየተከናወነ ነው፡፡ ባለስልጣኑ ለሙዚየሙ ህንፃ እድሳት ወደ 62 ሚሊዮን ብር የበጀተ ሲሆን የሙዚየሙን ምድረ ግቢ የማስዋብና ለማስፋፊያ ስራ ደግሞ 88 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
እድሳቱ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያትም ሙዚየሙ ረዥም እድሜ ያስቆጠረ መሆኑ አንደኛው ነው፡፡ ሌላው የፍሳሽ ማስወገጃው በተገቢው የተሰራ ባለመሆኑ ፍሳሽ ያስገባል፤ ግርግዳው ረጥቧል፤ ወይቧል፤ ሽታም አምጥቷል። ይህ ለቅርሶቹና ለህንፃው ስጋት በመሆኑ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ መታደስ አስፈልጓል፡፡ ጉዳት የደረሰበት የህንፃው ውጫዊ ግርግዳ እንደ አዲስ ተሰርቷል፡፡ የህንፃው ከመሬት በታች የሚገኘው ክፍል (ግራውንድ) ክፍል ውሃ ያስገባል፡፡ ይህን ለመከላከል የጡብ ግንብ ከመሬት ስር ተሰርቷል። የተሰባበሩ መስታወቶችን በአዲስ የመተካት፣ የዛጉ ብረቶችን የመቀየር፣ ጣራውን የመቀየርና ሌሎችም እየተከናወኑ ነው፡፡ በህንፃው ውጫዊ ክፍል በሙዚየሙ መግቢያ የተለያዩ የሞዛይክ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ የቀለም ቅቡም የከተማዋን ደረጃ በሚመጥን መልክ ይቀባል፡፡
አቶ ሀፍታሙ እንዳስረዱት፤ ሙዚየሙ አንጋፋ በመሆኑ ከሀገር ውስጥ ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ ህብረተሰቡ ከህፃናት እስከ አዋቂ እንዲሁም የውጭ ሃገር ጎብኚዎች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎችም የሚጎበኙት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ምድረ ግቢውን ሳቢና ማራኪ በማድረግ ተጨማሪ መሰረተ ልማቶች ተሟልተው ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡ ግቢው ጠባብ ቢሆንም ባለው ስፍራ የጎብኚዎች ማረፊያ፣ ፓርኪንግ፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ ፋውንቴን፣ ለህፃናት ማረፊያ፣ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መጠቀሚያ መንገድ የመለየት እና ሌሎች አካቶ እየተሰራ ነው፡፡
ሙዚየሙ በከፊል ለጎብኝዎች ሲሆን ቢሆንም እድሳቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ የሙዚየሙ ውስጣዊና ውጫዊ እንዲሁም ምድረ ግቢው ገፅታውን የተዋበ ያደርገዋል፡፡ ደረጃውን ከፍ ያደርገዋል። የጎብኚዎችን ቆይታ የሚያራዝምም ይሆናል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ሙዚየሙን በመጎብኘት ባህሉን፣ ታሪኩን እንዲያውቅ፣ ተመራማሪዎችም እንዲመራመሩ ሙዚየሙ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ሁሉም መጥቶ እንዲጎበኝ አቶ ሀፍታሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የትምህርት ዴክስ ኃላፊ አቶ ንጉሱ መኮንን በበኩላቸው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት መረጃ፤ ሙዚየሙ በርካታ ዓመታትን ያገለገለ በመሆኑ ፍሳሽ ስለሚያስገባ በውስጡ ላሉ ቅርሶችና ለህንፃው ስጋት ስለሆነ ቅርሶቹን ለመጠበቅ፤ የሙዚየሙን ውስጣዊና ውጫዊ ክፍል ደረጃውን ለማሻሻልና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ፣ ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሃ ቅርስ ለማስተዋወቅ ጥናት ተደርጎ እድሳት ተጀምሯል፡፡
በሌላ በኩል የግቢው የቦታ ጥበት፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን፣ ነፍሰጡሮች ተደራሽ ባደረገ መልኩ እንዲስተካከል ከህብረተሰቡ ጥቆማዎች ይደርሱን ነበር የሚሉት አቶ ንጉሱ እድሳቱ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩም እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
ሙዚየሙ አራት የቅርሶች አውደ ርዕይ ማሳያ ክፍል ያለው ሲሆን በ2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ድጋፍ ውስጣዊ ክፍሉ እድሳት ተደርጎለት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ የታሪክና የአርኪዮሎጂ ስብስብ ክፍሉ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታድሶ ተጠናቅቋል፡፡ በተጨማሪም ኤምባሲው የአርኪዎሎጂ ግኝቶች በተለይ የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ እና የእንስሳት ቅሪተ አካል የሚታይበትን ሉሲን ጨምሮ የምትገኝበት ሁለተኛው ክፍል ሙዚየሙን በሚመጥን ልክ ሃላፊነቱን ወስዶ ወጪውን በመሸፈን እድሳቱን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ ዓመት አጋማሽ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡ ቀሪዎቹ የብሔር፣ ብሔረሰቦች ባህል፣ አኗኗር፣ ታሪክ የሚታይበትና የሥነ ጥበብ ውጤቶች የሚታዩበት ሁለቱ ክፍሎች ደግሞ ፕሮጀክት ዲዛይኑ ተጠንቶ አስፈላጊ ነገር ተካቶ በሂደት የሚታደሱ መሆኑን አቶ ንጉሱ ገልፀዋል፡፡
የሙዚየሙ ውስጠኛው ክፍል እድሳቱ የሚከናወነው የቅርሶች ደህንነት እንዲጠበቅ፣ እንዳይበላሹ፣ አቧራ እንዳይቦንባቸውና ክፍሉ ለጎብኝዎች ምቹ እንዲሆንና ረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም የሙዚየሙ የመሬቱን ምንጣፍ በማንሳት የማስተካከል፣ ቅርሶች የሚቀመጡበትን ደረጃውን በጠበቀ መልክ ማደስ፣ የቅርሶች ማሳያ በአዲስ መልክ መቀየር፣ የቅርሶች ታሪክ የአዳዲስ ግኝቶች ጭምር የሚገልፁ ፅሁፎች ማካተት፣ በሙቀት ምክንያት ቅርሶች እንዳይበላሹ ማቀዝቀዣ (አይ ሲ) መግጠም፣ መብራት በአዲስ መልክ መቀየር፣ የህንፃውን ቀለም የከተማዋን ደረጃ በያዘ መልክ የመቀየር፣ ጣራው፣ ግርግዳውና ሌሎችም ተካተው ይዘቱን ጠብቆ እንደሚታደስ ነው አቶ ንጉሱ ያስረዱት፡፡
ሙዚየሙ ብዙ ቅርስና ታሪክ ይዟል፡፡ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ምድረ ግቢው ጠባብ በመሆኑ ሌሎች ተጨማሪ ሙዚየሞች በመዲናዋ እንዲሰሩ የረዥም ጊዜ አቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሙዚየም መንደር የኮሪደር ልማቱ አካል በመሆኑ ጎብኚዎች ከመስቀል አደባባይ፣ ከአዲስ አበባ ሙዚየም ጀምረው ወደ ሳይንስ ሙዚየም በመሄድ ቀጥታ ወደዚህ ሙዚየም እንዲመጡ በኮሪደር ስራው አማካኝነት የተሳሰረ በመሆኑ እንዲጎበኙት እድል ይዞ የመጣ ነውም ብለዋል፡፡
ሙዚየም ለህዝብ ነው የሚከፈተው። ከዚህ አንፃር ህዝቡ ባህሉንና ታሪኩን ማወቅ አለበት፡፡ ህብረተሰቡም የጉብኝት ልምዱን በማዳበር በአዲስ መልክ ይዘቱን ጠብቆ እየታደሰ በመሆኑ ከተጠናቀቀ በኋላ አዳዲስ ቅርሶችን፣ ታሪኮችን መጎብኘትና ማወቅ እንዳለበት አቶ ንጉሱ ያነሳሉ፡፡
በሙዚየሙ የሚገኙ ቅርሶች አውደ ርዕይ በአራቱም የሙዚየሙ ክፍሎች ይቀየራሉ፡፡ አዳዲስ ቅርሶች የሰው ዘር አመጣጥ የሚያሳዩ፣ የሰው ዘርና እንስሳት ቅሪተ አካል፣ የተለያዩ የድንጋይ መሳሪያዎችና ሌሎች ቅርሶች ለህዝብ እይታ ይቀርባሉ፡፡ የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበትን 50 ዓመት አስመልክቶም አዳዲስ አውደ ርዕዮች ይቀርባሉ፡፡ እድሳቱ ሲጠናቀቅ የሙዚየሙ ገፅታ የበለጠ ውበት ይኖረዋል። ይህም የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የቱሪስት ፍሰቱን ይጨምራል፡፡ ጥንታዊ ባህሎችና ታሪኮች፤ አሁናዊ ሁኔታዎች ለማስተዋወቅም ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑንም አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በቱሪዝሙ ዘርፍ በአዲስ አበባ ቀደምትና አንጋፋው የታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች መገኛ ስፍራ ነው፡፡ ሙዚየሙ ለጎብኚዎች ምቹ አገልግሎት መስጠት እንዲችል መታደሱ የሀገር ውስጥ እና በተለይ ደግሞ የውጭ ሃገር ጎብኚዎች የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያስችላል፡፡
ቅርሶች ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ፣ ትውልዱ በባህል፣ ታሪኩና ማንነቱ እንዲኮራ እና ከትናንት እንዲማር ትልቅ እድል ይፈጠራል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያን “ምድረ ቀደምት” ካሰኟት ቅርሶች መካከል አንዷ የሆነችውን 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን እድሜ ያላትን የሰው ልጅ ቅሪተ አካል (ሉሲ) እና ሌሎች ቅርሶችን የያዘው ሙዚየም መታደሱ ይበል የሚያሰኝ ነው እንላለን፡፡
በሰገነት አስማማው