AMN – ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም
ከቀኑ 6 ሰዓት አከባቢ በአዋሽ ፈንታሌ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰምቷል፡፡
ትናንት ምሽት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት በመዲናዋ አሁንም ዳግም መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ኤሊያስ ሌዊ (ዶ/ር) ለኢቢሲ አረጋግጠዋል።
ከቀኑ 6 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ9 ሰኮንድ በአዋሽ ፈንታሌ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ እነደሆነም ገልጸዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ሲሆን በአካባቢው ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴ አሁንም እንዳልቆመ ኤሊያስ ሌዊ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
አሁን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት መጠኑ አነስተኛ መሆኑን የገለፁት ኤሊያስ ሌዊ (ዶ/ር)፤ በአዋሽ ፈንታሌ እና ሳቡሬ ከተማ መካከል ላይ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡