ከተማ አስተዳደሩ የጣራ እና ግድግዳ ግብር የማስከፈል ስልጣን አለው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ከተማ አስተዳደሩ የጣራ እና ግድግዳ ግብር የማስከፈል ስልጣን አለው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ ያቀረቡትን የከተማ አስተዳደሩን የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ሀሳብና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ከንቲባዋ የጣራ እና ግድግዳ ግብርን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ የጣራ እና ግድግዳ ግብር አዋጅ በ1968 የወጣ አዋጅ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በዚያን ወቅት የነበረው አሰራር መቀጠሉን የገለጹት ከንቲባዋ ነገር ግን የተቀየረው ወቅቱን ያገናዘበ የዋጋ ተመን ነው ብለዋል፡፡

አዋጁ ሲወጣ የነበረው የኪራይ ዋጋ እና አሁን ያለው የኪራይ ዋጋ እኩል ባለመሆኑ አሁን የጨመረው ኪራዩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ከተማ አስተዳደሩ የሚያስከፍለው ግብር በትክክለኛ ዋጋው ሳይሆን ለመኖሪያ ቤት የዋጋውን ግማሽ እንዲሁም ለንግድ ቤቶች 75 በመቶ ብቻ እንደሆነም ከንቲባዋ አስታውቀዋል፡፡

በመዲናዋ በግብር ስርዓት ውስጥ ያልነበሩ በርካታ ነዋሪዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች በከተማዋ ካሉ 800 ሺ ህንጻዎች እና ቤቶች ግብር ይከፍሉ የነበሩት 120 ሺ ብቻ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጣራ እና ግድግዳ ግብር የመሰብሰብ በአዋጅ የተሰጠ ስልጣን ያለው መሆኑን እና ግብር እንዳይሰበስብ ያገደው ህጋዊ አካል አለመኖሩንም ከንቲባዋ አስታውቀዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review