21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም አቀፍ ከተሞች ፈጣን ለውጥ አምጥቷል። በብዙ መልኩ ተራርቀው የነበሩ ከተሞች የተቀራረቡ፣ ዘላቂነት ያላቸው እና በቴክኖሎጂ የሚመሩ ማዕከላት እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ ወቅት በከተሞች መካከል ያለው የለውጥ አብዮት እጅግ እየፈጠነ ስለመሆኑም “የስማርት ከተማ አብዮት” በተሰኘው የማርክ ዴኪን እና ሁሳም አል ዋየር ጥናታዊ መፅሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡
እንደ መፅሐፉ ከሆነ የቴክኖሎጂ እድገት በከተማ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በዚህም ምክንያት “የስልጡን (ስማርት) ከተሞች” ዕድገት በእጅጉ አየተፋጠነ መሆኑምተመላክቷል፡፡ እነዚህ ስማርት ከተሞች ብልህ (ስልጡን) የመጓጓዣ ዘዴዎች፣ ዘላቂ የኃይል መፍትሄዎች (የታዳሽ ሃይል አማራጮች)፣ በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዙ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎች ያሏቸው ሲሆን፣ በኮሪደር ልማትም ሆነ በሌሎች ዘመኑን የዋጁ ስራዎች የተሻለ በመከወናቸው ለነዋሪዎቻቸውም ሆነ ለእንግዶቻቸው ምቹ ከተሞች መሆን ችለዋል፡፡ እንደ ሲንጋፖር፣ ባርሴሎና እና አምስተርዳም ያሉ ከተሞች የኮሪደር ልማትን በመሳሰሉ ዘርፎች በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ ልማትን ቀድመው በመጀመራቸው ሌሎች የአለማችን ከተሞች የእነርሱን ፈለግ እንዲከተሉ መንገድ ስለመጥረጋቸውም በመፅሐፉ ተመላክቷል፡፡
በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የከተሞች ዕድገት ሁለንተናዊ ዘላቂነትን እና አረንጓዴ መሠረተ ልማትን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ ለአብነትም ለከተማ ግብርና እና መሰል አረንጓዴ ቦታዎች፣ ፓርኮች፣ መናፈሻዎች እና በአረንጓዴ ልማት ለታጀቡ መንገዶች ሰፊ ትኩረት በመስጠት ከውበት ባሻገር ሰርተዋል። ለምሳሌ፣ ኮፐንሃገን እ.ኤ.አ በ2025 በዓለም የመጀመሪያዋ ከካርበን ነፃ የሆነች ማዕከል ለመሆን እየሰራች እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ አዲስ አበባ ከተማም ይህንን የሰለጠነ መንገድ በመከተል ላይ ስለመሆኗም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
“ጤናማ ከተማ እንዴት እንገንባ?” በተሰኘው የዊልያም ኤች. መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የከተማ ፕላን እና የህዝብ ጤና የጠበቀ ትስስር ያላቸው በመሆኑ በኮሪደር ልማትም ሆነ መሰል የከተሞች እንቅስቃሴ ውስጥ በዋናነት ታሳቢ ይደረጋሉ፡፡

በኮሪደር ልማትና መሰል ተግባራት ከተማን ማዘመን ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ እና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ሙህዲን ሙሐመድ እንደገለፁት በየትኛውም ሁኔታ፣ ከፍታና ዝቅታም ውስጥ ቢሆኑ ከተሞች ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ስኬታማነት ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ስማርት መሆን ከከተማዋ ሁለንተናዊ ከፍታ ባሻገር እንደ ሀገር ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እምርታ የሚያመጣ ነው ብለዋል፡፡
የመጀመሪያው የሰው ልጅ ስልጣኔ የዛሬ 6 ሺህ ዓመት አካባቢ ከተሞችን ማዕከል አድርጎ መፈጠሩን ያስታወሱት መምህሩ፣ ይህ ማለት ከተሞች ከመፈጠራቸው በፊት ሰዎች በተበታተነ ሁኔታ ይኖሩ ነበር፡፡ በመሆኑም ለከተሞች መፈጠር ምክንያት የሆነው የሰው ልጅ ስብስብ ነው፡፡ የሰው ልጅ እንዲሰባሰብ ያደረገውም ዋናው ምክንያት በተናጠል ምልዑ ስላልሆነ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠረው የሰዎች ስብስብ እርስ በእርስ የተለያዩ መስተጋብሮች እንዲኖሩ ያደርጋል። ለአብነትም ንግድ፣ መሰረተ ልማት እና የተለያዩ ፈጠራዎች ይስፋፋሉ። መሰረተ ልማቱ እየተስፋፋ ሲሄድ ከተለያዩ ቦታዎች ሰዎች ወደዚህ አካባቢ ይመጣሉ፡፡ አዲስ ለሚመጣው ኃይል ደግሞ መልስ ለመስጠት ሲባል ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ይኖራሉ። ከተሞች በዚህ ዘመን ላይ የስልጣኔ፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ማዕከል ናቸው። በመሆኑም ከተማን ከስልጣኔ፣ ከዕድገት፣ ከልማት እና መሰል ዘመናዊ ነገሮች ልንለይ አንችልም ብለዋል፡፡
እንደ መምህር ሙህዲን ስለ ስማርት ሲቲዎች ስናነሳ ከዚህ ቀደም ባልሄድንበት መንገድ ነው የምንሄደው ብለን ማየት አለብን፡፡ ለአብነትም አዲስ አበባን ብንወስድ የኢትዮጵያ የስልጣኔ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ መስተጋብር የፖለቲካ እና የተለያዩ ጉዳዮች ማዕከል ናት። እዚህ ላይ ስማርት ሲቲን ስናስብ ብዙ ዕድሎችን ይሰጠናል። ይሄውም ከተማዋ ስማርት ስትሆን ዜጎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው አፈፃፀም እንዲጨምር፣ ብክነት እንዳይኖር እና አገልግሎት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን፣ ቀልጣፋ ውሳኔ ለመስጥ፣ ዜጎችንም በተሻለ ሁኔታ ለማሳተፍና ፍላጎታቸውንም ለማሟላት ያስችላል ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱም ሆነ በሌሎች ተግባራት ከተማዋ ስማርት ስትሆን ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በሁሉም ዘርፍ ለመጠቀም ትችላለች፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የአገልግሎት ተደራሽነት ይሰፋል። ቅልጥፍናውም ይጨምራል፡፡
የህንድን መንገድ ለአብነት የጠቀሱት መምህር ሙህዲን፣ ሀገሪቱ አገልግሎትን ማዕከል አድርጋ ትንቀሳቀሳለች። አገልግሎት ማዕከል ሲሆን ደግሞ በዋናነት አይ.ሲ.ቲን የሚጠቀም ነው፡፡ በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፍ በትኩረት ይሰሩበታል፡፡ በዚህም የከተማ ዕድገትና ገቢ የህዝብ ተጠቃሚነትና የአገልግሎት እርካታ በዚያው ልክ እያደገ እንደሚሄድም ተናግረዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞችም ስማርት ሲቲ መሆናቸው በቅርባችን ካሉ የሌሎች ሀገራት ከተሞች አንፃር የተሻለ ተወዳዳሪ እንድትሆን እና ከፍ ብላ እንድትወጣም ያደርጋታል ያሉት መምህር ሙህዲን፣ በተለይ አዲስ አበባ በምስራቅ አፍሪካ፣ በቀጣናው እና እንደ አህጉር ያላትን ከፍታ ለማስቀጠል ስማርት መሆን ግድ ይላታል፤ በኮሪደር ልማቱም ሆነ በሌሎች ዘርፎች እየታዩ ያሉ ለውጦች ይህንን የሚያመላክቱ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡
በዓለማችን እነ ፓሪስን የመሳሰሉ ከተሞች አሁን ያሉበት ደረጃ የደረሱት እንዲህ በቀላሉ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የፓሪሱ የኤፍል ታወር ግንባታ እ.ኤ.አ በጥር 1887 ተጀምሮ በመጋቢት 1889 የተጠናቀቀ ቢሆንም በግንባታው ወቅት በአካባቢው ነዋሪዎች አዎንታዊ እና አሉታዊ ውዝግቦች ተፈጥረው ነበር፡፡
አንዳንድ የፓሪስ ነዋሪዎች የግንባታውን ዲዛይን ከከተማው ውበት ጋር የማይጣጣም እና ቀልብን የማይገዛ ሲሉ ተችተውት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የማማው ልዩ ንድፍ የፓሪስ እና የፈረንሳይ ተምሳሌት ሆኗል። ዛሬ የኤፍል ታወር በዓለም ላይ በብዛት ከሚጎበኙ የቱሪስት መስህቦች አንዱ እና የፓሪስ ማንነት መገለጫ ነው። በሲዊዲን እና መሰል ሀገራትም ከተሞቻቸውን ሲገነቡ እንዲህ በቀላሉ አይደለም፤ ውድ ዋጋ ተከፍሎባቸው ነው ስማርት መሆን የቻሉት፡፡
የኒውዮርክ ከተማ ብዙ ጊዜ በኮሪደር ልማት እንደ ስኬታማ ምሳሌ ትጠቀሳለች፤ በተለይም ሰፊ የምድር ውስጥ ባቡር እና ዘመናዊው የአውቶቡስ መስመር ስሟን በበጎ ከሚያስጠሩ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። የከተማዋ “የምስራቅ ወንዝ ኮሪደር” እና ሌሎች የተለያዩ የከተማ ፕላን ውጥኖች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ረገድ ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡
የኮሪደር ልማት በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በሩቅ ምስራቅ፣ ላቲን አሜሪካና በአፍሪካ የሚገኙ ከተሞች መልሰው የሚለሙበት፣ ቀድሞ የነበሩ ስህተቶች የሚታረሙበት ወይም የሚስተካከሉበት የከተማ ልማት ሞዴል እንደሆነ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ይናገራሉ። በመንገድ ግራና ቀኝ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያ፣ የንግድ፣ ቢሮዎችን ጨምሮ ሁሉንም አገልግሎቶች የያዘ፣ 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥና ዘላቂነት ያለው ከተማ የሚገነባበት የከተማ ልማት ነው፡፡
የኮሪደር ልማት ቅርብ ጊዜ ብቅ ያለአስተሳሰብ (Emerging Concept) ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ልማት ከግል ተሽከርካሪ ይልቅ የብዙሃን ትራንስፖርት አማራጮችን የሚያበረታታ፣ ለእግረኞች ዕድል የሚሰጥ፣ ንግድንና የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያበረታታ፣ የንግድ፣ መኖሪያ፣ የቢሮ ህንጻዎች አካትቶ የሚይዝ ነው፡፡ ሰዎች በአንድ ቦታ የሚኖሩበት፣ የሚሰሩበት፣ የሚፈልጉትን የሚሸምቱበትና የሚሸጡበት ውብና አረንጓዴ የከተማ አካባቢ ለመፍጠር የሚያግዝ የልማት ዓይነት እንደሆነ ነው ዳንኤል (ዶ/ር) የገለጹት፡፡

የኮሪደር ልማት በዋናነት ሶስት መሰረታዊ ጥቅሞች (“3D”) እንዳሉት ዳንኤል (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ አንደኛው ጥግግት (Density) ሲሆን በትንሽ ቦታ ብዙ ሰው እንዲኖር በማስቻል ውጤታማነትን (efficiency) ያሳድጋል። ውጤታማ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ስርዓትን ያመጣል፡፡ ብዝሃነት (Diversity) ሁለተኛው ባህሪይ ሲሆን የዘር፣ ቋንቋና ሌሎችን ልዩነቶችን ሳይለይ የሚያቅፍ፣ የመሬት አጠቃቀሙ ቅይጥ (የንግድ፣ የመኖሪያ፣ የቢሮ አካባቢ) እና ብክነትን የማያስከትል ነው፡፡ ሶስተኛው ከርቀት (Distance) አኳያ ያለው ጠቀሜታ ሲሆን ይህም ማለት ሰዎች በአንድ አካባቢ የሚኖሩና የሚነግዱ ከሆነ አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት ሳይሄዱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ማለት ነው። ረጅም ርቀት ስለማይሄዱም የግል መኪና መጠቀም አያስፈልጋቸውም፤ መሄድ ከፈለጉም እንደ ባስ፣ ባቡር ያሉ የብዙሃን ትራንስፖርት መጓጓዣዎችን ይጠቀማሉ ማለት ነው፡፡
ዳንኤል (ዶ/ር) እንደሚሉት የኮሪደር ልማት የሚከናወንባቸው ቦታዎች የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን የጀርባ አጥንቶች ናቸው። የዋና ዋና መንገዶች የደም ስሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መስመሮች የመዝናኛ፣ የንግድና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት የተጨናነቁ አካባቢዎች እንደመሆናቸው መለወጣቸው በብዙ መልኩ የከተማዋን ችግር ይቀርፋሉ፡፡ አዲስ አበባን ስናይ አንዳንድ አካባቢዎች ቀን ላይ ሞቅ ደመቅ ያሉ ሆነው ማታ አስፈሪ ድባብ ያለባቸው ናቸው፡፡ ብዙ የአፍሪካ ከተሞች ማታ ላይ ጨለማ ሆነው ይታያሉ፡፡ ኮሪደሩ የበለጠ ሲለማ 24 ሰዓት የንግድና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንባት ከተማ ትሆናለች፡፡ ሰው ቀንና ሌሊት ይሰራል፤ ኢንቨስትመንትን ይስባል። 24 ሰዓት እንቅስቃሴ ባለበት ከተማ ደግሞ ወንጀልም ይቀንሳል፡፡ ሰርቶ የሚኖርና ልማት ላይ የሚያተኩር አመለካከት ህዝብ ይፈጠራል ይላሉ ዳንኤል (ዶ/ር)፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ ሰዎች የሚዝናኑባቸው በቂ ስፍራዎች የሉም፡፡ የልጆችና አረጋዊያን ወዳጅ ከተማ አይደለችም የሚሉት ዳንኤል (ዶ/ር) የኮሪደር ልማቱ አረንጓዴ ቦታዎችን የሚያካትት በመሆኑ ችግሩን እያቃለለው ነው፡፡ ይህ ልማት አዲስ አበባን የመኖሪያ፣ የንግድ፣ የመዝናኛና የቱሪዝም መስህብ ከተማ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። የኮሪደር ልማቱ ስማርት የሆነች አዲስ አበባን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡ ስማርት ሲቲ ሲባል ብልህ የሆነች ከተማ መፍጠር ማለት ነው፡፡ ለኑሮ ምቹ የሆኑና ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሱ ከተሞች በሄዱበት አካሄድ በሳይንስና በስታንዳርድ የምትመራ ከተማ ነው የምትሆነው። ሁሉም ኮሪደር ሲለማ የትራፊክ ፍሰቱ፣ የመሬት አስተዳደሩን ጨምሮ እያንዳንዱ አገልግሎትና እንቅስቃሴ ስማርት ይሆናል፡፡ የመጪው ትውልድም የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
በመለሰ ተሰጋ