AMN – ጥር 20/2017 ዓ.ም
ከተናጥል ትርክት ይልቅ የጋራ ፤አሰባሳቢ የወል ትርክት ላይ በማተኮር አገርን ወደ ከፍታ ማሻገር ይገባል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡
አቶ ሞገስ ባልቻ የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤን አስመልክተው ማብሪያ ሰጥተዋል
በሀገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ትርክት ጽንፍ ላይ የተመሰረተ እና ልዩነት ላይ አነጣጥሮ ይሰራ የነበረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህም ለዕርስ በዕርስ ግጭት መነሳሳትን የጋበዘ እና ለዛሬው የኢትዮጵያ ዋነኛ ምክንያት ፈተና መሆኑን አውስተዋል፡፡
ይህንን ሊያክም የሚችል አስታራቂ እና የሀገሪቱን ሁኔታ እና የፖለቲካ አኗኗር እና ስሪት መሰረት ያደረገ እንዲሁም የህዝቡን ሁኔታ ያማከለ ትርክት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አብሮ የኖረ ፣የተጋመደ፣ ለአገር ሉዓላዊነት በአንድ አብሮ የተዋደቀ ህዝብ ያለባት አገር በመሆኗ የተናጥል ትርክትን በመተው እና የጋራ ፤አሰባሳቢ የወል ትርክት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በጋራ ስንቆም አቅሞቻችንን እና ጸጋዎቻችንን በመጠቀም አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንችላለን ብለዋል በማብራሪያቸው
በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ አንድ መድረክና አመለካከት መምጣት እንደሚኖርበት አንስተዋል፡፡
የጋራ እና የወል ትርክትን ብንገነባ አገራችንን ማሻገር እና ወደ ትልቅ ደረጃ ማድረስ የምንችልበት ሁኔታ ይፈጠራልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በግጭት እና በደም መፋሰስ ውስጥ ያለፈች እና ይህም ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈላትም አውስተዋል
ይህንን የሰላም እጦት ማከም እና ሰላምን ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ስብራቶችን በማቃናት አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ላይ በትኩረት መስራት ይገባናል የሚለውን አንስተዋል፡፡
ይህን መሰረት በማድረግም ብልጽግና የሄደበት ርቀት አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑንና ለተሻለ ውጤት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጭምር አቶ ሞገስ አብራርተዋል።
በሰለሞን በቀለ