የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ማምሻውን ከስሎቬኒያ ፕሬዜዳንት ከዶ/ር ናታሻ ፒርስ ሙሳር ጋር በመሆን ፒኮክ የከተማችን ግዙፉ ፓርክ ውስጥ ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ሰርቶ ማሳያ (Urban Beeking Observatory) ስራ በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።
ከተማችን አዲስ አበባ የነዋሪዎቿን ህይወት ማሻሻል ላይ ያተኮረ ሰፊ ለውጥ እያስመዘገበች ይገኛል ፤የከተማ ግብርና የዚህ አጀንዳ ቁልፍ ምሰሶ ነው። ይህም የምግብ ዋስትናን ማዕከል ያደረገ የአረንጓዴ ልማት ማስፋፋትን ይጨምራል ብለዋል።
ፕሮጀክቶችን በተሳካ መልኩ በማከናወን የህዝባችንን ኑሮ ለመለወጥ ያስችለን ዘንድ ከአለም አቀፍ አጋሮች፣ ኤምባሲዎች እና ሀገሮች ጋር በንቃት አብረን እንሰራለን።
ለአብነትም ዛሬ ከፕሬዝዳንቷ ጋር በመሆን በይፋ ስራ ያስጀመርነው ፒኮክ የከተማ የንብ ማነቢያ ሰርቶ ማሳያ አንዱ ሲሆን ስሎቬንያ በከተማ ንብ እርባታ የላቀ ልምድ ያላት በመሆኗ ይበልጥ ትብብራችንን ለማጠናከር እንሰራለን።
ልምዳቸዉን በማጋራትና ሀገር በቀል እሳቤያችን ለመደገፍ ወስነው ተጨባጭ ስራ በመጀመራቸው ፕሬዚዳንት ናታሻ እና በኢትዮጵያ የስሎቬኒያ አምባሳደር የሆኑትን ክርስቲና ራዴጅ ከልብ አመሰግናለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላልፈዋል።