
AMN – ህዳር 7/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማለዳ ከቦሌ ካርጎ እስከ ቡልቡላ አቃቂ ድልድይ ድረስ ተገንብተው ለነዋሪዎች አገልግሎት ክፍት የተደረጉ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
በቦሌ ክፍለከተማ እየተገነባ ያለውን 13 ኪ.ሜ የሚሸፍን የአረንጓዴ ልማት ስራ ተዘዋውረው የጎበኙት ከንቲባዋ ይህም አራት ዘመናዊ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች፣ ሁለት የህጻናት የመጫዎቻ ሜዳዎች፣ አንድ የስፖርት ሜዳ፣ አምስት ዘመናዊ የህዝብ መገልገያ የጋራ መጸዳጃ ቤቶች፣ ደረጃውን የጠበቀ ሰፊ የእግረኞች መንገድ፣ በከተማው ስታንዳርድ መሰረት የተከናወኑ የህንጻዎች እድሳት፣ ፋውንቴኖች፣ የመዝናኛ ፓርኮች እንዲሁም የህዝብ መናፈሻ ቦታዎች የተካተቱበት መሆኑ ተመላክቷል።
ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን በመደገፍ ይህን ስራ ያሳኩ የቦሌ ክፍለከተማ አመራሮች፣ ድጋፍ ያደረጉ ባለሀብቶች እንዲሁም ለአካባቢው ነዋሪዎች ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከልና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የምናከናውናቸውን ስራዎችን ከነዋሪዎቻችንን ጋር በመተባበር መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉም ገልጸዋል።