
AMN-ግንቦት 19/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ የሱፍን እንኳን ደህና መጡ ብለው ተቀብለው ማነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከንቲባዋ ቆይታቸውን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከኮሚሸነር አሊ የሱፍ ጋር በተለያዪ የልማት እና የአፍሪካ ከተሞች ትብብርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ስለ ቀጣይ ስራዎች የአዲስ አበባ ድርሻ እና አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ፣ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቶች ከተማ በመሆኗ ኩራት የሚሰማት በመሆኑ እስከ አሁን እያገለገለች ካለችዉ በላይ ሁሉንም ነዋሪዎቿን እና ተቀማጭ ዲፕሎማት እንግዶቿን ባማከለ መልኩ በትጋት ለማገልገል ሀላፊነቷን በተሟላ ሁኔታ ለመወጣት እየተጋች እንደሆነ ገልፀንላቸዋል ሲሉም አስፍረዋል።

ሊቀመንበሩ አዲስ አበባን ተዟዙረው መመልከታቸውን፣ በበአላት እና ምሽት ጭምር የአዲስ ለአበባ ነዋሪዎች የሥራ ባህል ለውጥ ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውንም ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ለውጥ በሌሎች የአፍሪካ ከተሞችም እንዲስፋፋ ተሞክሮዎችን መቀመር እንደሚገባም ገልፀዋል ነው ያሉት።