ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ልጆች አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ትልቅ ተግባር ነው- ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

You are currently viewing ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ልጆች አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ትልቅ ተግባር ነው- ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

AMN- መጋቢት 14/2017 ዓ.ም

ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ልጆች የትምህርት ማዕድ፣ የጤና ክብካቤ እና የስራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ትልቅ ተግባር ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡

የዓለም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጀው 5ኛው “መጋቢትን ከዲቦራ ጋር” የእግር ጉዞ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው።

በመርሐ-ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ልጆች የትምህርት ማዕድ፣ የጤና ክብካቤ እና የስራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ትልቅ ተግባር ነው ብለዋል።

የአንድ ማህበረሰብ ታላቅነት የሚገለጸው በመጠበቡ ደረጃ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ፣ የኢትዮጵያውያን ታላቅነት መገለጫው ለመሰል ህጻናት በምንሰጠው ትኩረት እና ድጋፍ ይለካል ሲሉም ተናግረዋል።

ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር የተወለዱ ልጆችን ስሜት መጋራት እና በነርሱ ቦታ ሆኖ ማሰብ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ልጆች መጀመሪያ ፍቅር ልንሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የማድረግ ኃላፊነት አለብን ሲሉም አክለዋል።

ይህንንም በቅንጅታዊ አሰራር ማሳካት እንደሚቻል ነው የገለጹት።

በዚሁ መሰረት ከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን ለልጆች የተመቸች ከተማ ለማድረግ በርካታ ስራዎች አከናውኗል ብለዋል።

የሰለጠኑ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ተጠቂዎችን በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የስራ እድል እንደሚፈጠርላቸውም ገልጸዋል።

የዲቦራ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ቤኪ አባዱላ፣ ዲቦራ ፋውንዴሽን ለሌሎች መድረስ አልሞ የተቋቀመ መሆነኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ግንዛቤ ለመፍጠር እና መቻልን ለማሳየት የተመሠረተ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዳውንሰንድረም ጋር የተወለዱ ህጻናት እንደሚችሉ ለማሳየት እና የሚገባቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

ፋውንዴሽኑን እየደገፉ ለሚገኙ ተቋማት እና ግለሰቦችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራች አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፣ ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር የተወለዱ ልጆች ሰርተው መለወጥ የሚችሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ 60 ሰልጥነው ስራ የሚጠብቁ ህጻናት ዜጎች እንዳሉ ገልጸዋል።

አባዱላ አክለውም ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር የተወለዱ ልጆችን መቅረብ ፍቅርን መሸመት መሆኑን ገልጸው፣ የተለያዩ ተቋማት የሰለጠኑ ልጆችን ለመቅጠር ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ልጆችን መደገፍ እና አቅማቸውን እንዲያሳዩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም በቂ ህክምና እና እንክብካቤም ያስፈልጋቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና እነርሱን ያማከለ ስረዓት መዘርጋት ጀምረናል ነገር ግን የበለጠ ማጠናከር ይገባል በማለትም አስገንዝበዋል።

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review