በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተዘጋጀው ውስን ዓላማ ባላቸው የድጎማ በጀቶች ትልልፍና በጋራ ገቢዎች ክፍፍል ላይ ያተኮረ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በውይይት መድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሁለቱ ከከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችና ሚኒስትሮች ታድመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በውይይቱ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፣ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሎች መካከል ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለመፍጠር የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በዚህም ከአገራዊ ለውጡ በፊት አራት ቢሊዮን ብር የነበረው የክልሎች የጋራ ገቢ የበጀት ክፍፍል አሁን ላይ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አንስተዋል።
የድጎማ በጀት ስርጭትን ግልፅና ፍትሃዊ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውንና በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል።
በውስን ዓላማ ባላቸው ድጎማዎች የአሰራር ግልፀኝነትና የአተገባበር ክፍተት ላይ የሚነሱ ውስንነቶችን ለመፍታትም የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን አመልክተዋል።
የክልል መንግስታት ከፌዴራል መንግስት ስለሚደረግላቸው ድጎማ ለሚመለከታቸው ተቋማት በግልፅ ማሳወቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በመድረኩ በውስን ዓላማ የድጎማ በጀቶች ትልልፍ እንዲሁም በከፍተኛ ማዕድን አምራች ድርጅቶች የሚገኙ የሮያሊቲ ገቢዎች ክፍፍል ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸዉ ኢዜአ ዘግቧል፡፡