AMN- መስከረም 29/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጠቅላላ ጉባዔው ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ይከናወናል።
የጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች ከአህጉራዊ ሁነቱ ጎን ለጎን በመዲናዋ የሚገኙ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ይጎበኛሉ።
የአዲስ አበባ፣ ብሔራዊ (አደይ አበባ)፣ አበበ በቂላ እና አቃቂ ዞናል ስታዲየሞች ከሚጎበኙት መሰረተ ልማቶች መካከል ይገኙበታል።
በተጨማሪም በየክፍለ ከተማው እየለሙ የሚገኙ አነስተኛ ስታዲየሞች (Mini stadiums) እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደሚጎበኙ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
ሌላኛው መርሃ ግብር ጉባዔን በማስመልከት የሚካሄድ የወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን ለጨዋታው አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የወዳጅነት ጨዋታው ከካፍ አመራሮች እና ከአባል አገራት በተውጣጣ ቡድን እና በአንጋፋ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች መካከል ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ መታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ 46ኛው ጠቅላላ ጉባዔ እንድታስተናግድ በመስከረም ወር መጀመሪያ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል።
ጉባዔው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ሀገሪቱ ማስተናገድ እንደማትችል ማሳወቋን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማካሄድ ያቀረበችውን ጥያቄ ካፍ አጽድቋል።