ከኮሌጁ የፈለቀው ፈጠራ

You are currently viewing ከኮሌጁ የፈለቀው ፈጠራ

የሰው ልጆችን ድካም የሚያቃልሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደየዘመኑ እየተሻሻሉ በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ዓለም ላይ በዘርፉ ያሉ ሰዎች በዚህ ረገድ ሰፊ ርቀት እየተጓዙ የማይቻል የሚመስለውን እንደሚቻል እያሳዩ ነው፡፡ ሀገራችን ለዚህ የቴክኖሎጂ እድገት እየሰጠችው ያለው ምላሽ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል፡፡ በተለይ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሠሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪዎች ናቸው፡፡

በርካቶችን የሙያ ባለቤት ካደረጉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት መካከል የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተጠቃሽ ነው፡፡ ኮሌጁ በበርካታ የትምህርት መስኮች ስልጠናዎችን ለተማሪዎቹ ይሰጣል፡፡ ችግር ፈቺ ብሎም ሀገር ከጎደላት ላይ የሚሞላ ትውልድን በማብቃት ረገድ ትልቅ አበርክቶን ከቸሩት መካከል የጠቅላላ መካኒክስ ሥልጠና ክፍል አሰልጣኞች እየሠሩ ያሉት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች በምሳሌነት ይነሳሉ፡፡

በጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የጠቅላላ መካኒክስ ሥልጠና ክፍል አሰልጣኝ የሆኑት ወርቁ ፋንታሁን እና ዘካሪያስ ምንዳዬ የመኖ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ለተጠቃሚዎች እነሆ ብለዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑን በመጠቀም ለእንሰሳት መኖ በማምረት ለተጠቃሚዎች ምርቶችን እስከማቅረብ የደረሰ ተግባር አከናውነዋል፡፡

አሰልጣኝ ወርቁ በማብራሪያቸው፤ “በኮሌጁ ውስጥ ከሚገኙት የሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን የመኖ ማቀነባበሪያ፤ የእህል መውቂያ፣ የሳሙና እንዲሁም የግራይንደር ማሽኖችን ለማምረት ችለናል፡፡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት በስፋት እየተተገበረ ያለው የከተማ ግብርና ስራ ደጋፊ አንድ አካል የሆነው የመኖ አቅርቦት ነው፡፡ አንድ በከተማ ግብርና ዘርፍ ተሰማርቶ የሚሠራ አካል አንስሳትን ለማደለብ፣ የወተት ምርትን ለማሻሻል እንዲሁም የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በስፋት ምርት እንዲሰጡ ለማስቻል በዋናነት ከእንስሳት ምርት ጋር በተያያዘ የመኖ አቅርቦት ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የእንሰሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑን ሠርተን ለአገልግሎት ለማብቃት ችለናል” ብለዋል፡፡

በኮሌጁ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ፒ ኤል ሲ) ሥራ አስኪያጅ አቶ አበጀ በለጠ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፤ ቴክኖሎጂዎችን ከመፍጠር ባሻገር ለአገልግሎት እንዲበቁ እና የማህበረሰቡን ድካም እንዲያቀሉ ለተጠቃሚ ማድረስ የኮሌጁ ተቀዳሚ ዓላማ ነው። የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት አጠቃላይ ዓላማ ብቃት ያለው፣ ተነሳሽነትን የተላበሰ፣ ለሥራ ፈጠራ የተዘጋጀና ከለውጥ ጋር ራሱን ማስተካከል የሚችል የሰው ኃይል በመፍጠር የከተማውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማፋጠን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ አበጀ አክለው እንዳብራሩት፤ ተቋማት ከመደበኛና አጫጭር ስልጠና መስጠት ባሻገር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች መፈልፈያ ማዕከል ማድረግ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል አቅም መገንቢያ እንዲሆኑ ማስቻልን እንደ ዓላማ በመያዝ የሚሠሩ ሲሆን፤ ይህም ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ የኢንተርፕራይዞችን አቅም ከሚያሳድጉ ተግባራት መካከል የቴክኖሎጂዎች ሽግግር አንዱ ነው። በኮሌጁ የተሠሩ በርካታ የምርትና የማምረቻ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ኢንተርፕራይዞቹ ተሸጋግረው  የምርት ዕድገታቸው፣ ጥራታቸው እና ፍጥነታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ የውጪ ምንዛሬ ከማስቀረት ባሻገር ዜጎች ሀገራዊ ምርቶችን እንዲያመርቱና የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ አበርክቷቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በኮሌጁ ሁለት ባለሙያዎች አማካኝነት የተሠራው የእንሰሳት መኖ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ ወደ አገልግሎት በመግባቱ ሁለት ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ  ሲያብራሩ፤ በቅድሚያ ማሽኑ በመሠራቱ በኮሌጁ የሚገኙ እንሰሳት በተመጣጣኝ ዋጋና በጥራት የተቀነባበረ መኖ እንዲያገኙ ረድቷል። እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩና በከተማው ዙሪያ ለሚገኙ የእንሰሳት መኖ ፈላጊ አካላት ጭምር በጥራት አምርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ገበያ በመግባት የኮሌጁን የውስጥ ገቢ አቅም ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሌላኛው ጠቀሜታ ደግሞ የእንሰሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑ በኮሌጁ እንዲመረትላቸው እያደረጉ ያሉ ኢንተርፕራይዞች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ የውስጥ አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ ከሚገኝባቸው የምርትና አገልግሎት መስጫ ተግባሩ ውስጥ አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡   

በጠቅላላ መካኒክስ ስልጠና ክፍል አሰልጣኞች ተሠርቶ ለአገልግሎት የበቃው የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን፤ በ2016 ዓ.ም የተሠራ ሲሆን ሙሉ ስራውን ለማጠናቀቅ የሁለት ወር ጊዜ መፍጀቱን በቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራው ላይ የተሳተፈው አሰልጣኝ ወርቁ ተናግሯል፡፡ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ማሽነሪዎች በዋናነት የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው በመጠቆም፤ ይህንን የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ከውጭ እናስገባ ብንል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ይጠይቃል፡፡ በኮሌጁ የተሠራውን ማሽን ግን ለተጠቃሚዎች በ6 መቶ ሺህ ብር እያስረከበ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

አሰልጣኝ ወርቁ፤ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑን እርሱ እና ጓደኛው ዘካርያስ ለመሥራት የተነሳሱበት ዋነኛ ምክንያት፤ በኮሌጁ ውስጥ 50 ላሞች አሉ፡፡ ላሞቹ ተገቢውን መኖ በተቀመጠላቸው የመመገቢያ ሰዓት መመገብ ካልቻሉ የሚፈለገውን ያክል የወተት ምርት መስጠት አይችሉም፡፡ ከዚህ ቀደም ለከብቶቹ መኖ ይጠቀሙ የነበረው ከውጭ በመግዛት ነው፡፡ አሁን ግን የመኖ አቅርቦት እጥረት እንደ ከተማችን ተጨባጭ ሁኔታ መኖሩን ተከትሎ ክፍተቱን ለመሙላት በቅጥር ግቢው ውስጥ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑን በመጠቀም በተመጣጣኝ ዋጋ ፍላጎቱን እያሟላ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ አሰልጣኝ ወርቁ ገለፃ፤ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በተመለከተ እንዲሁ ጤናማ እና በባለሙያ የተመጠነ መኖ እንዲያገኙ በማስቻል ጥራቱን የጠበቀ እንቁላል እንዲጥሉ አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ የወተት ላሞችም ጥራቱን የጠበቀ መኖ ማግኘት በመቻላቸው ምክንያት አንድም ጤናቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከማስቻሉ ባሻገር የምርት መጠናቸው የጨመረ እንዲሆን አስችሏል፡፡

በአሁን ሰዓት የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑ በቀን ከ20 እስከ 30 ኩንታል የማምረት አቅም አለው፡፡ የመኖ ዝግጅቱን በተመለከተ በቆሎ፣ ፉሩሽካ፣ፕሪሚክስ ወይም ቫይታሚን፣ ፋጉሎ፣ ጨው፣ የኖራ ድንጋይ እና መሰል ግብዓቶችን በሚገባ በመቀላቀል ይሰራል፡፡ መኖ የሚገዙት ብዙ ጊዜ በከተማ ግብርና የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ናቸው፡፡ አንድ መቶ ኩንታል የእንስሳት መኖ ከ3 ሺህ 500 ብር ጀምሮ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ወርቁና ጓደኛው የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑ ላይ በየጊዜው ምን ማሻሻል ይቻላል? የሚለውን በማጤን የተጠቃሚውን እርካታ ለመጨመር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ማሽነሪውን አንድ አካል ከገዛ በኋላ እንዴት ነው አገልግሎት የሚሰጠው? የሚለው ትምህርት ይሰጠዋል፡፡ ስለማሽነሪው በቂ እውቀት ካገኘ በኋላ ነው ጥቅም ላይ የሚያውለው፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ይቻላል፡፡ በተለይም ሀገራችን አሁን ላይ እየተከተለች ያለችውን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ ትልቅ አበርክቶ አለውም ብለዋል፡፡

አቶ አበጀም በማጠቃለያቸው ሲያስረዱ፤ በኮሌጁ የሚገኙ አሰልጣኞች ሚናቸው እጅጉን የላቀ ነው፡፡ ትምህርቱ 30 በመቶ የንድፈ ሃሳብ፣ 70 በመቶ ደግሞ የተግባር በመሆኑ እንዴት ስራዎችን መከወን ይቻላል የሚለውን በቀላሉ ሰልጣኞች እንዲረዱት ያግዛቸዋል፡፡ ኮሌጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አባዝቶ ይሸጣል፡፡ አባዝቶ መሸጥ ብቻ ሳይሆን የምርት እጥረቶች ሲገጥሙ እንደ እንስሳት መኖ ብሎም የፅዳት እቃዎችን አምርቶ ለተጠቃሚዎች ያደርሳል፡፡ እነዚህ ስራዎች ጅምር ናቸው፡፡ ብዙ ስራዎችን የመስራት ጥሩ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ኮሌጁ አሉት ብለዋል፡፡

የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽነሪው እጅግ አስፈላጊ ብሎም እንደ ከተማ ያለውን የመኖ እጥረት ሊያስታግስ የሚችል ከመሆኑ ባሻገር የኮሌጁን የውስጥ ገቢ ማሳደግ የቻለ  ነው፡፡ ይህንን መሰሉ ቴክኖሎጂ ወደ ገበያ መግባት መቻሉ ከእንስሳቱ የምናገኘውን ምርት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሁም ጤናማ እንዲሆን ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review