AMN-ኅዳር 28/2017 ዓ.ም
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ካሳንችስ አካባቢ እየለማ ባለው የኮሪደር ልማት የሚነሱ 350 የልማት ተነሺዎች ምትክ ቤት እጣ አወጡ።
የእጣ አወጣጡም ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ በቴክኖሎጂ ተደግፎ ለነዋሪዎቹ ይፋ ተደርጓል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዳስ አበባ አተማ የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወ/ገብርኤል፣ አዲስ አበባ ከተማን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት መነሻውን ከአራዳ ክፍለ ከተማ ማድረጉን በማስታወስ በዚህ ውስጥ ለተባበሩት የክፍለ ከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኮሪደር ልማቱ ዋና ዓላማ ከተማዋን ውብ እና ጽዱ ማድረግ መሆኑን ያነሱት ኃላፊዋ ልማቱ የነዋሪውን ህይወትም እየቀየረ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የእጣ አወጣጡ ከሰው እጅ ንክኪ በጸዳ መልኩ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ፍትሐዊ ያደርገዋል ብለዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ በበኩላቸው፣ በኮሪደር ልማት ምክንያት በመጀመሪያ ዙር ከ100 በላይ የልማት ተነሺዎች ከዚህ ቀደም ይኖሩበት ከነበረ ያልተመቸ ስፍራ ወደ ምቹ ቦታ ተዘዋውረዋል ብለዋል።
በዚህ ዙርም 350 የሚሆኑ የክፍለ ከተማዋ ነዋሪዎች ማህበራዊ መስተጋብራቸው ሳይስተጓጎል ወደ ተመቻቸላቸው ስፍራ እንዲዛወሩ እጣ ማውጣታቸውንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል።
በአፈወርቅ አለሙ