AMN-ታህሳስ 18/2017 ዓ.ም
ኦሮሚያ ክልልን ከግጭት ወደ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ተናገሩ፡፡
በኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እና ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር የተዘጋጀው 40ኛዉ ጉሚ በለል የውይይት መድረክ “ከግጭት አዙሪት ወደ ዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ፣ ክልሉን ከግጭቶች ወደ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለማሸጋገር በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጦርነት ችግር ፈቺ አለመሆኑን ሁሉም ተረድቷል ያሉት አቶ ሀይሉ ህዝቡ በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ እንደቆየ አስታውሰዋል።
የጦርነት ምዕራፍን በእርቅ እና ይቅርታ ለማጠናቀቅ ሁሉም ኃላፊነት አለበት ሲሉም ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩ የኦሮሞ ቀዬ ሰላም እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው የተጀመረው የሰላም መንገድ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሃብታሙ ሙለታ