ወርሃዊ የሃይል ፍጆታ ሂሳብን ለማስላት እና ለምን እንደሚከፍሉ ለማወቅ ከዚህ በታች የተገለጸውን የአሰራር ቀመር ይጠቀሙ፡፡
አንድ የመኖሪያ ቤት ደንበኛ ወርሃዊ የሃይል የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ ሲከፍል የአገልግሎት ክፍያ፣ የተቆጣጣሪ ባለስልጣን የሚከፈል የቁጥጥር ቀረጥ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ለኢቲቪ የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያ እና የአገልግሎት ክፍያ ተጨማሪ እሴት ታክስ የያዘ ነው፡፡
አሠራሩም ደንበኞች በወር ውስጥ የተጠቀሙት የኃይል ፍጆታ ሲባዛ ወቅታዊ የአንድ ኪዋሰ ታሪፍ ማባዣ እና ከላይ የተዘረዘሩትን ክፍያዎችን የሚያጠቃልል ነው፡፡
ለምሳሌ ከጥር እስከ መጋቢት ከ400 እስከ 500 ኪዋሰ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም አንድ ደንበኛ የአንድ ኪዋሰ ወቅታዊ የታሪፍ ማባዣ መጠን 3.73 ብር ነው።
በዚህ መሰረት ደንበኛችን በወር ውስጥ 450 ኪዋሰ ተጠቅመዋል ብለን ብናስብ፡-
1. ወርሃዊ የሃይል ፍጆታ=450 ኪ.ዋ.ሰ* 3.73 ብር (ወቅታዊ የታሪፍ ማባዣ)= 1678.5 ብር፣
2. የአገልግሎት ክፍያ / ከ50 ኪ.ዋ.ሰ በላይ ፍጆታ ለሚጠቀሙ ደንበኞች/=44.85 ብር /፣
3. የአገልግሎት ክፍያ ተጨማሪ እሴት ታክስ=የአገልግሎት ክፍያ*15% ይህም ማለት 44.85 ብር *15%=6.7275 ብር፣
4. ለተቆጣጣሪ ባለስልጣን የሚከፈል ቀረጥ/= (ወርሃዊ የሃይል ፍጆታ+የአገልግሎት ክፍያ) 0.5% ይህም ማለት ((450*3.73) + 44.85) 0.5%=8.616፣
5. ተጨማሪ እሴት ታክስ /VAT/ ክፍያ= (ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳብ x ወቅታዊ የታሪፍ ማባዣ)15% ይህም ማለት (450 ኪ.ዋ.ሰ*3.73)15%=251.775፣
6. ከ50 ኪ.ዋ.ሰ በላይ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቲቪ) የሚከፈል 10 ብር.
በመሆኑም ከላይ ባለው አሠራር መሰረት የደንበኛችን ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ክፍያ ወርሃዊ የሃይል ፍጆታ (1678.5ብር)+የአገልግሎት ክፍያ (44.85 ብር)+የአገልግሎት ክፍያ ተጨማሪ እሴት ታክስ (6.7275 ብር)+የቁጥጥር ባለስልጣን ቀረጥ (8.616 ብር)+ የተጨማሪ እሴት ታክስ (251.775 ብር )+ ለኢቲቪ የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያ (10 ብር) በአጠቃላይ 2000.468 ብር ይሆናል፡፡
በመጨረሻም ከላይ ባለው ቀመር የፍጆታ ሂሳብ ክፍያዎን ማስላት የሚችሉ መሆኑን እያሳወቅን፤ ከወቅታዊ የታሪፍ ስሌት ጋር ተያይዞ ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኝት ከታች ያያያዝነውን ምስል መመልከት በማለት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃውን አካፍሏል፡፡