AMN- የካቲት 16/ 2017 ዓ.ም
የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ (AYLDC) የመክፈቻ ስነሥርዓት በስካይ ላይት ሆቴል ተካሄዷል።
ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር (EYDPA) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መሆኑ ተገልጿል።
የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ፣ ያለሰላም ጠንካሪ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ፈጠራንና ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን በመድረኩ ገልፀዋል።
ወጣቶች ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድ ሊያዳብሩ እና በሰላም ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚናቸውን ሊጫወቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የምንመኛትን የበለፀገችና አንድነቷ የተረጋገጠ አፍሪካ እውን ለማድረግ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን ሊጠቀሙና በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም በአመራርነት ላይ ያሉ ወጣቶችን በማበረታታትና ሁሉን አቀፍ ተሳትፏኣቸውን በማረጋገጥ አህጉሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል።
የፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ አቀንቃኙ ፕሮፌሰር ፓትሪስ ሉሙቧ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የነገዋ አፍሪካ እጣ ፈንታ የሚወሰነው አሁን ላይ ባሉ ወጣቶች እንደሆነ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የወደፊት የለውጥ መሪዎች እና ወኪሎች የሆኑት የአፍሪካ ወጣቶች በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ በጋራ የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽዕኖት ሰጥተዋል።
ኮንፈረንሱ ስለአመራርነት፣ ስለዲፕሎማሲ እና ስለ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት፣ ስለፈጠራ ሰፊ ውይይት ለማካሄድ ያለመ እንደሆነ የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ዳይሬክተር ወጣት ኢንጂነር ጫላ አሰፋ ገልጿል።
ኮንፈረንሱ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በመድረኩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ ዩኒቨርስቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣት መሪዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።