የ35 ዓመቷ ቻይናዊት አቢ ዉ ውበቷን ለማጎላት ከ100 ጊዜ በላይ የመዋቢያ ቀዶ ጥገና አድርጋለች፡፡
አቢ ዉ ባለፉት 21 ዓመታት ይሄ ቀረሽ የማትባል “የደም ገምቦ’’ ለመሆን ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ለቀዶ ጥገና አውጥታለች፡፡
ቻይናዊቷ እንስት ለመጀመሪያ ጊዜ የመዋቢያ ቀዶ ጥገና (cosmetic surgery) ያደረገችው የ14 ዓመት ኮረዳ እያለች ነበር፡፡
አቢ ዉ በወቅቱ አጋጥሟት ለነበረው ህመም በተደረገላት የሆርሞን ሕክምና ክብደቷ ከ42 ኪሎ ግራም ወደ 62 ኪሎ ግራም ይጨምራል፡፡
ክብደት መጨመሯ በድራማ መምህርቷ ዘንድ ያልተወደደላት አቢ ዉ ፤ መምህርቷ “አንቺ ኮኮባችን ነበርሽ ፤ አሁን ግን በጣም በመወፈርሽ ተዋናይ በመሆን ህልምሽ ተስፋ ልትቆርጪ አሊያም ክብደት ልትቀንሺ ይገባል’’ ይሏታል፡፡
በዚህ ጊዜ ወላጅ እናቷ “ላይፖሳክሽን” በመባል የሚታወቀውን በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ስብን በቀዶ ጥገና የመቀነስ ህክምና ወደሚሰጥበት ሆስፒታል ይወስዷታል፡፡
“ጀግና ሁነሽ አንዴ ግቢ እንጂ ከቀዶ ጥገና ክፍሉ የምትወጪው ውብ ሆነሽ ነው” የአቢ ዉ እናት የመጨረሻ የማበረታቻ ቃላቶች ነበሩ፡፡
ከሆድ እና እግሯ አካባቢ ስብን መጥጦ በማውጣት የተጀመረው የቻይናዊቷ “የውበት ፈርጥ” የመሆን የቀዶ ጥገና ጉዞ ፤ እንደ ውኃ እያባበላት ከ100 ጊዜ በላይ ሰርጀሪ ወደማድረግ እንዳደረሳትም ለቢቢሲ ተናግራለች፡፡
ቻይናዊቷ እንስት በአሁኑ ሰዓት በማዕከላዊ ቤጂንግ የሚገኘ ስመ ጥር የውበት ክሊኒክ ባለቤት ስትሆን ፊቷም ከፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ጋር በተያያዘ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሆኗል፡፡
በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ቻይናውያን የውበት ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡