
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ፍትሕን፣ እኩልነትን አለፍ ሲልም ጀግንነትን በዓለም አደባባይ ያስመሰከረች፡፡ ነፃነቷን አስከብራ ለብዙዎች የነፃነት መውጫ በር የሆነች:: ለዚህ ደግሞ የዓለም የእኩልነትና የታሪክ ሚዛኑ የዓድዋ ድል በቂ ምስክር ነው፡፡ የዓድዋ ድልን ተከትሎም በዘመኑ የነበሩ ኃያላን ሀገራት በኢትዮጵያ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል፡፡ የሩሲያ ግን ከዚህም ከፍ ይላል፡፡
የታሪክ ድርሳናት እንደሚመሰክሩት በዚያ ጠላትና ወዳጅ በሚለይበት ዘመን የሩሲያ ቀይ መስቀል ማህበር አባላት በዓድዋ ጦርነት ማግሥት የኢትዮጵያ ጀግኖችን ቁስል በማከም ዘመን የማይሽረው ፍቅራቸውን ገልፀዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የደጃዝማች ባልቻ መታሰቢያ ሆስፒታል የታሪክ ምስክር ነው፡፡ በርግጥ የሀገራቱ የግንኙነት ታሪክ ብዙ ዘመናትን ወደ ኋላ ያስጉዘናል፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍታና ወዝ እንደተጠበቀ ዘልቋል፡፡
በትናንትናው ዕለትም ሩሲያ የሁለተኛውን ዓለም ጦርነት 80ኛ የድል በዓልን በሞስኮ በሚገኘው ቀዩ አደባባይ በደማቅ ወታደራዊ ትርዒት አክብራለች። ኢትዮጵያም ዘመን የተሻገረ አጋርነቷን በሚያስመሰክር መልኩ በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተወክላ ተገኝታለች፡፡ ለፕሬዝዳንቱ የተደረገላቸውም ከፍ ያለ አቀባበል የሀገራቱን ጠንካራና ዘመን የተሻገረ ግንኙነት ይመሰክራል፡፡
ይህ ታላቅ ትዕይንት “ሶቪየት ኅብረት” በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት “በናዚ” ላይ ድል መቀዳጀቷን የሚያስታውስ እና ሩሲያውያን ልዩ የሀገር ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ነው። ሰልፉ ከድል መታሰቢያነቱ ባሻገርም እንደ ብሔራዊ የመታሰቢያ ቀን የሚታይም ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ80ኛው የሩሲያ የድል በዓል ለሚሳተፉ የሀገራት መሪዎች በበዓሉ ዋዜማ በክሬምሊን ቤተ-መንግስት በተካሄደው የአቀባበል እና የእራት ግብዣ ስነ ስርዓት ላይም ተሳትፈዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በያዝነው ዓመት የካቲት ወር ላይ ከሩሲያ ፌዴሬሽን የፌዴራል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቫለንቲና ማትቪዬንኮ ጋር መወያየታቸው አይዘነጋም፡፡ ታዲያ በዚሁ ወቅት የኢትዮ-ሩሲያ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎሚሲ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግርም፣ የኢትዮጵያና ሩሲያን የታሪክ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትና ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገዋል። ኢትዮጵያና ሩሲያ በመርህ ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ታሪካዊ ትብብር ያላቸው ሀገራት ናቸው ማለታቸውም ይታወሳል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ፣ ትምህርት፣ ባህል እንዲሁም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስኮች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። በተለይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢኮኖሚው መስክ ጠንካራ ግንኙነት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆናቸውን መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እና ሩሲያ አጋርነት ከሶቪየት ኅብረት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬው የሩሲያ ፌዴሬሽን ድረስ በፅናት የተሻገረ ነው፡፡ ሀገራቱ በየዘመኑ የተለያዩ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ የተወሰኑትን እንኳ ብንጠቅስ በዲፕሎማሲ፣ በመከላከያ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ፣ በንግድ እና መሰል ዘርፎች በየዘመኑ እየጎለበተ የመጣ ነው፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ይህ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ እየጎመራ ስለመምጣቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከሀገራቱ የቅርብ ጊዜያት ታላላቅ ዲፕሎማሲያዊ ትስስሮች መካከል አንዱን በዋቢነት ብናነሳ ብሪክስን እናገኛለን። በደቡብ አፍሪካዋ የንግድ መዲና ጆሃንስበርግ 15ኛውን ጉባኤያቸውን ያካሄዱት የብሪክስ ሀገራት ኢትዮጵያን አዲስ የስብስቡ አባል አድርገው መቀበላቸው አይዘነጋም፡፡
ታዲያ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ከሩሲያ እና መሰል ታላላቅ ሀገራት ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ የረጅም ዘመናት የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርገዋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል ሀገር መሆኗ በሀገራቱ ያለውን ኢንቨስትመንት ለመሳብ ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡
በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በተለያዩ ዘርፎች ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል። በተለይም እ.ኤ.አ በ2021 ሁለቱ ሀገራት የኢትዮጵያን የመከላከያ አቅም፣ በእውቀት ሽግግር እና በቴክኖሎጂ ማሳደግ ላይ ያተኮረ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል። በተጨማሪም ሩሲያ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ተሳትፎ በማድረግ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ስኮላርሺፕ እና የአካዳሚክ ልውውጥ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ፣ ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ተፅዕኖ ለማስፋት ካላት ፍላጎት ጋር ተዳምሮ የመተባበራቸውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የጎላ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ግንኙነት በታሪካዊ ትስስር እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ አጋርነት ያለው ስለመሆኑም የፖለቲካል ሳይንስ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
የታሪክ ድርሳናት እንደሚመሰክሩት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት በዋነኝነት በኢትዮጵያ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የተለያዩ የሩሲያ ሰዎች ከኢትዮጵያ የተለያየ የግዕዝ መዛግብትን ይዘው ወደ ሩሲያ ሄደዋል። ሩሲያውያኑ በሀገራቸው የግዕዝን ቋንቋ እስከ ማስተማርም ደርሰዋል፡፡

ትናንት የተከበረው የሩሲያ የድል ቀን 80ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ የ20 ሀገራት መሪዎች ታድመውበታል። የድል በዓሉ በሞስኮ አደባባዮች በተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶች እንዲሁም የጦርነቱ ሰማዕታትን በማሰብ ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ልዩ ዝግጅት የኦርሺኒክ እና አር ኤስ 28 አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች እና ሌሎች ዘመናዊ ትጥቆችም ለእይታ ቀርበውበታል፡፡
የሩሲያ ኤር ስፔስ፣ ታንክ፣ ዘመናዊ ተሸከርካሪዎች እና ሌሎች ወታደራዊ ክፍሎች ትርዒት ያቀረቡ ሲሆን በሞስኮ ሬድ ስኩዌር በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ፕሬዚዳንት ፑቲን ባደረጉት ንግግር፣ ሀገራቸው ሩሲያ ጠልነትን መዋጋቷን ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሀያላኑ የበርካታ ሀገራትን ግዛት በማለፍ በደሎችን ሲፈጽሙ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ይህንን በደል በወቅቱ የነበረው የሶቭየት ሀይል መቀልበስ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ድሉ ሩሲያ ያላትን ሀቅ ለዓለም ያሳየችበት እንደበር ገልፀው፤ ሊጨቁኑ የመጡትን ኃይሎች በመፋለም አባት ሀገር ላስረከቡን ጀግኖቹ የሶቭየት ወታደሮች ምስጋና ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
ሩሲያ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ሁልጊዜ እንደምታስታውስ የገለፁት ቭላድሚር ፑቲን፣ ሆኖም ግን ታሪክን ለማዛባት የተለያዩ አካላት በሚያነሱት ሀሳብ አንስማማም ነው ያሉት፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጦር ላይ ድል የተቀዳጁ የሩሲያ ወታደሮች ለዘለዓለም በታሪክ ውስጥ ሲታሰቡ እንደሚኖሩም በአፅንኦት ገልፀዋል። በናዚ ጦር ሽንፈት ውስጥ የተለያዩ ሀገራት እና የተባበሩት መንግስታት መሳተፋቸውን አስታውሰው፣ ሩሲያ ይህን ፈፅሞ አትረሳም ብለዋል።
በመለሰ ተሰጋ