AMN – ጥር 9/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የ2017 ዓ.ም 2ኛው ዙር እጩ የሰላም ሰራዊት አባላትን አስመርቋል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ ባለፉት የለውጥ አመታት በጸጥታው ዘርፍ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የሰላም ሰራዊት አባላት እና የህዝቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሰላም ሰራዊቱ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ቀን ከሌት እንዲሰሩም አደራ ብለዋል።
ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚከበሩ የከተራ እና ጥምቀት በአላት በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የገለጹት ኮሚሽነሩ የዛሬ ተመራቂዎችም ይህንን ስራ በመደገፍ ለበዓሉ ስኬት የራሳቸውን አስተዋጽዖ ማበርከት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
የሰላም ሰራዊቱ በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ ልማቶችን የመጠበቅ እና ማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፣ በበጀት አመቱ ለሁለተኛ ዙር የተመረቁ የሰላም ሰራዊት አባላት ለጸጥታ ሀይሉ አጋዥ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ የላቀ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።

ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ረገድ የሰላም ሰራዊት የላቀ አበርክቶ ያለው በመሆኑ ይህንን መሰረት በማድረግ ተመራቂዎች ጠንካራ የህግ አስከባሪ አካል ሊሆኑ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ኃላፊዋ አክለውም በ2ኛው ዙር የተመረቁ የሰላም ሰራዊት አባላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የከተማዋን ሰላም እንዲያስጠብቁም አደራ ብለዋል።

በሐብታሙ ሙለታ